ቀጥታ፡

ህዝበ ክርስቲያኑ ለአገር አንድነትና ሰላም መስፈን ሊሰራ እንደሚገባ ተጠየቀ

ጅማ ታህሳስ 23/2011 ህዝበ ክርስቲያኑ ለአገር አንድነትና ሰላም መስፈን ከምንጊዜውም በላይ በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ የቅዱስ ሲኖዶስ የሰላም ልዑካን ቡድን አባላት አሳሰቡ።

የሰላም ልዑካን ቡድን አባላት ይህንን ያሉት ከጅማ፣ ከየምና ከኮንታ ሀገረ ስብከት ጋር በመተባበር  በአገራዊ አንድነትና ሰላም ላይ ያተኮረ ጉባዔ ባለፉት ሶስት ቀናት በጅማ ከተማ ባካሄዱበት ወቅት ነው፡፡

የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት  ጉባኤ የቦርድ አባል ክቡር ንቡረ ዕድ ኤልያስ አብረሃ በጉባኤው ላይ እንዳሉት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አገራዊ የሰላምና አንድነት መረሃ ግብር ዘርግታ ተግባራዊ እያደረገች ነው።

የአገር ሰላምና አንድነት ከሃይማኖት ስራ ተለይቶ አይታይም ያሉት የቦርድ አባሉ ህዝበ ክርስቲያኑ ለአገር አንድነትና ሰላም መስፈን የዕለት ተዕለት ተግባሩ ከማድረግ ባለፈ የህይወቱ መርህ ሊሆን እንደሚገባው አስገንዝበዋል።

በመንበረ ፓትሪያሪክ ጠቅላይ ቤተክህነት የሰበካ ጉባኤ ማደረጃ ምክትል መምሪያ ኃላፊ ሊቀ ትጉሃን ታጋይ ታደለ በበኩላቸው ሲኖዶሱ የሰላምና አንድነት አጀንዳ በመያዝ በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር በሚገኙ 88 ሀገረ ስብከቶች ውስጥ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ሰው ከራሱ ጋር ሲጣላ በተፈጥሮ ላይ ጭምር  በክፋት ይዘምታል የሚሉት ሊቀ ትጉሃን ሁሉም ከራሱ ጋር በመታረቅ ለአገር ሰላምና አንድነት የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያደረግ አሳስበዋል።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የጅማ፣ የየምና የኮንታ ሀገረ ስብከት ሊቀጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ብፅዕ አቡነ እስጢፋኖስ ጉባዔው ሀገረ ስብከቱ በቀጣይ ለሚያካሄደው አገልግሎት ስኬታማነት ጉልህ ድርሻ እንዳለው አመልክተዋል።

የጎማ አጋሮ ወረዳ ቤተክህነት ኃላፊ  መላአከ ገነት ዘውዴ ካሴ በሰጡት አስተያየት በአገር ላይ ጉዳት የሚያመጣ ችግር ሲከሰት የሁሉም እምነት ተቋማት ችግሩን በችለተኝነት መመልከት የለባቸውም።

"አባቶች ለወጣቶች ሥነ ምግባር ተጠያቂ ወይም ተመስጋኝ ነን" ያሉት መላአከ ገነት ዘውዴ የሃይማኖት አባቶች የተጣለባቸውን ኃላፊነት በአግባቡ ሊወጡ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

በጉባዔው ላይ ከጅማ ዞን የተውጣጡ የሀገር ሽማግሌዎች፣ መምህራን፣ ሊቀካህናትና ዲያቆናት ተሳትፈዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም