ቀጥታ፡

የእግር ኳስ ክለቦቹ በሜዳቸው ያቋረጡትን ውድድር እንደገና ሊጀምሩ ነው

ባህር ዳር ታህሳስ 23/2011 የአማራና የትግራይ እግር ኳስ ክለቦች በሜዳቸው ያቋረጡትን ውድድር እንደገና ለማስጀመር ዝግጅት መጠናቀቁን የአማራ ክልል መንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ገለጸ።

ሰሞኑን የፋሲል እግር ኳስ ክለብ ቡድን ከመቀሌ አቻው ጋር ለመጫወት ወደመቀሌ እንደሚያመራም ተመልክቷል።

የጽህፈት ቤቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ አሰማኽኝ አስረስ ዛሬ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ በሁለቱ ቡድኖች ደጋፊዎች መካከልተፈጥሮ በነበረው ግጭት ክለቦቹ ላለፈው አንድ ዓመት ከሜዳቸው ውጭ በገለልተኛ ሜዳ ውድድራቸውን ሲያካሂዱ ቆይተዋል።

በእዚህም የእግር ኳስ ክለቦቹ በሜዳቸውና በደጋፊዎቻቸው ፊት መጫወት ካለመቻላቸው በተጨማሪ በውጤታቸው ላይ ተጽዕኖ ማሳደሩንና በሜዳቸው ከተመልካች ያገኙት የነበረውን ገቢ አሳጥቷቸው መቆየቱን ገልጸዋል።

አቶ አሰማኽኝ እንዳሉት ችግሩን በመፍታት ክለቦቹ በመርሃ ግብራቸው መሰረት በሜዳቸው እንዲጫወቱ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ከሁለቱም ክልሎች ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ጋር ውይይት ሲያደርግ ቆይቷል።

"ሁለቱ ክልሎች የደረሱትን ስምምነት ተከትሎም ክለቦቹ ለአንድ ዓመት ያህል በሜዳቸው አቋርጠውት የነበረን ውድድር እንደገና እንዲጀምሩ የጋራ መግባባት ላይ ደርሰዋል" ብለዋል።

የክልሉ መንግስትም ውድድሮችን ሰላማዊ በሆነ መልኩ ለማካሄድ በክልሉ ከሚገኙ የእግር ኳስ ደጋፊ ማህበራት፣ ከክለብ አመራሮችና ተጫዋቾች፣ ከሃይማኖት አባቶች፣ ከሀገር ሽማግሌዎችና ከፀጥታ ኃይሉ ጋር ተከታታይ ውይይቶችን ማድረጉን ተናግረዋል።

ስፖርት የፖለቲካ ማራመጃ እንዳልሆነ ሁሉም አምኖ ውድድሮች ስፖርታዊ ጨዋነት በተላበሰ መልኩ እንዲከናወኑ የጋራ መግባባት ላይ መደረሱንም አመልክተዋል።

" ክለቦቹ በመርሀ ግብሩ መሰረት ውድድራቸውን በሜዳቸውና በደጋፊዎቻቸው ፊት እንዲያደርጉ በተደረሰው ስምምነት መሰረት ሰሞኑን የፋሲል እግር ኳስ ክለብ ቡድን ወደ መቀሌ ይሄዳል " ብለዋል።

በቀጣይም የሽሬ ስሑል እግር ኳስ ቡድን ወደባህር ዳር በመምጣት ውድድሩን ከባህር ዳር እግር ኳስ ቡድን ጋር እንደሚያደርግም አስረድተዋል።

የእግር ኳስ ቡድኑ ወደ ባህር ዳር ሲመጣም ህብረተሰቡና ወጣቱ ለእግር ኳስ ቡድኑ የእንኳን ደህና መጣችሁ አቀባበል እንደሚደረግለትም አስረድተዋል።

የትግራይ ክልል እግር ኳስ ቡድኖች ከአማራ ክልል አቻወቻቸው ጋር ለመጫወት በሚመጡበት ጊዜ ምንም አይነት የፀጥታ ችግር እንዳይገጥማቸው በቂ ዝግጅት መደረጉንም አቶ አሰማኽኝ አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም