ቀጥታ፡

በጣና ሐይቅ በተከሰተ የጀልባ መስጠም አደጋ የ12 ሰዎች ሕይወት አለፈ

ባህር ዳር  ታህሳስ 23/2011 በጣና ሐይቅ በተከሰተ የአነስተኛ ጀልባ መስጠም አደጋ የ12 ሰዎች ሕይወት ማለፉን የባህር ዳር ዙሪያ ወረዳ ፖሊስ ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ ኮማንደር ንብረት ሞላ ለኢዜአ እንደገለጹት ጀልባዋ የመስጠም አደጋ የደረሰባት በባህር ዳር ዙሪያ ከምትገኘውና "ልጆሚ" ተብላ ከምትጠራ ቀበሌ ተነስታ ወደ ደቅ ደሴት እያመራች ባለችበት ወቅት ነው።

ጀልባዋ ከሰዎች በተጨማሪ ከፍተኛ ክብደት ያለው የማገዶ እንጨትና ከሰል ጭና መጓጓዟ ለመስጠሟ አንድ ምክንያት መሆኑን ኮማንደር ንብረት ገልጸዋል።

በወቅቱ ከፍተኛ የሆነ ሞገድ ተነስቶ እንደነበር ከአካባቢው ነዋሪዎች ማረጋገጥ እንደተቻለ የጠቀሱት ኮማንደሩ፣ ጉዞው በጨለማ መሆኑም የነብስ አድን ሥራውን በወቅቱ ለማከናወን አለመቻሉን አስረድተዋል።

ኮማንደር ንብረት እንዳሉት ታህሳስ 21 ቀን 2011 ዓ.ም ከንጋቱ 11፡ 00 አካባቢበተከሰተው የጀልባ መስጠም አደጋም በጀልባዋ ላይ ተሳፍረው የነበሩ 12 ሰዎች ሕይወት ያለፈ ሲሆን እስካሁን  የአንዲት ሴት አስከሬን ተገኝቷል።

የቀሪ ሟቾችን አስከሬን የሟች ዘመዶችንና የአካባቢውን ማህበረሰብ በማሳተፍ የማፈላለግ ሥራው መቀጠሉንም አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም