ሰላምና ልማትን የሚያደናቅፍ ማናቸውንም ኃይል በጋራ ለመታገል ቁርጠኛ መሆናቸውን የኢህአዴግ ወጣት ሊግ አባላት ገለጹ - ኢዜአ አማርኛ
ሰላምና ልማትን የሚያደናቅፍ ማናቸውንም ኃይል በጋራ ለመታገል ቁርጠኛ መሆናቸውን የኢህአዴግ ወጣት ሊግ አባላት ገለጹ
መቀሌ ታህሳስ 22/2011 በአገሪቱ ሰላምና ልማትን የሚያደናቅፍ ማናቸውንም ኃይል በጋራ ለመታገል ቁርጠኛ መሆናቸውን የኢህአዴግ ወጣት ሊግ አባላት ገለጹ፡፡
ዛሬ በመቀሌ ከተማ በተጠናቀቀው የህወሓት ወጣት ሊግ አራተኛ መደበኛ ጉባኤ ላይ የእህት ደርጅት ወጣቶች በመገኘት አጋርነታቸውን አረጋግጠዋል፡፡
የኢህአደግ ወጣት ሊግ ምክትል ሊቀመንብር ወጣት አክሊሉ ታደሰ እንዳለው የትግራይ ወጣት ለዘላቂ ሰላምና ልማት የሚያደርገውን ትግል ሁሉም ወጣት ሊከተለው ይገባል።
በተለይ ህዝብን ከህዝብ የሚያጋጩና ልማትን የሚያወድሙ ኃይሎችን በተደራጀ መንገድ መታገል የወጣቱ ሚና መሆኑም አስታውቋል፡፡
ከደኢህዴን ወጣት ሊግ አመራር የተወከለው ወጣት ገዘሀኝ መጎ በበኩሉ የህዝብ ሰላምና የአገር ልማትን ለማደናቀፍ እየሰሩ ያሉ ኃይሎችን በቁርጠኝነት ለመታገል እንደሚሰራ ነው የገለጸው።
በትግራይ ክልል ሰላምን ዘላቂ ለማድረግ እየተሰራ ያለውን ሥራ በቀጣይ በክልላቸው ለመተግበር እንደሚሰራም ተናግሯል፡፡
" እኛ ወጣቶች ሰላምና ልማት እንጂ ሁከትና ግርግር አንፈልግም " ያለው ደግሞ የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኦዴፓ) ወጣት ሊግ ሊቀመንበር ወጣት ሃሰን ሞሳ ነው፡፡
በሀገሪቱ ሰላምና ልማትን አጠናክሮ ለማስቀጠል ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል በተለይ ወጣቱ በጋራ ሊታገል እንደሚገባና ለእዚህም ዝግጁ መሆኑን ተናግሯል፡፡
የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዴፓ) ወጣት ሊግ አመራር አባል ወጣት ተሾመ ፋንታው በበኩሉ በደምና በአጥንት የተሳሰረ የአማራና የትግራይ ህዝብን ለማለያየት የሚደረግን ጥረት እንደሚያወግዘው ገልጿል፡፡
በባህልና በታሪክ የተሳሰሩ ሁለቱን ህዝቦች ለማለያየት በማህበራዊ ትስስር ሚድያ በተቀናጀና በተደራጀ መንግድ የሚደረግ ዘመቻን ከሌሎች ወጣቶች ጋር በመሆን እንደሚታገል አረጋግጧል፡፡
የአገርን ልማትና የህዝብ ተጠቃሚነትን ወደ ኋላ ከሚጎትት ማናቸውም ተግባር የተቆጠበ ወጣት እንዲኖር በሚደረገው ጥረት የበኩሉን እገዛ እንደሚያደርግም ወጣት ተሾመ ተናግሯል፡፡
ላለፉት ሦስት ቀናት በመቀሌ ከተማ በተካሄደውና ዛሬ በተጠናቀቀው የህወሓት ወጣት ሊግ አራተኛ መደበኛ ጉባኤ ላይ 700 ወጣቶች መሳተፋቸው ታውቋል።