የቻይና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ከነገ በስቲያ ኢትዮጵያ ይገባሉ

79

አዲስ አበባ ታህሳስ 22/2011 የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ዪ ከነገ በስቲያ ጀምሮ በኢትዮጵያ የስራ ጉብኝት ያደርጋሉ።

ሚኒስትሩ በኢትዮጵያ ጉብኝት ሲያደርጉ በስድስት ወር ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ ነው።

በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ በተደረገላቸው ግብዣ መሰረት ዋንግ ዪ ሰኔ 14 ቀን 2010 ዓ.ም በኢትዮጵያ ጉብኝት ማድረጋቸው ይታወሳል።

ሚኒስትሩ በኢትዮጵያ በሚኖራቸው ቆይታ ከፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ፣ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ እና ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ ጋር ውይይት እንደሚያደርጉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።

የጉብኝታቸው ዓላማ በሁለቱ አገሮች መካከል ያለውን ሁሉን አቀፍ ስትራቴጂያዊ ትብብር ለማስቀጠልና ወደላቀ ደረጃ ለማሳደግ ያለመ ነው ተብሏል።

ሁለቱ አገሮች ከግንቦት 2009 ዓም ጀምሮ ግንኙነታቸውን ወደ ሁሉን አቀፍ ስትራቴጂያዊ ትብብር ማሳደጋቸው ይታወቃል።

ትብብሩም በሁለትዮሽ፣ በባለብዙ ወገን፣ በህዝብ ለህዝብ፣ በንግዱ ማህበረሰብ እና በሌሎችም የተደገፈና ሁሉን አቀፍ እንደሆነ ይገለጻል።

ኢትዮጵያ እና ቻይና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የጀመሩት በ1960ዎቹ ሲሆን ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በሁለትዮሸ እና በባለብዙ ወገን ጉዳዮች በትብብር በመስራት ላይ ይገኛሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም