የመዲናዋን ሁለቱ ዝነኛ ክለቦች ያገናኘው ጨዋታ ያለግብ ተጠናቀቀ

97

አዲስ አበባ ታህሳስ 21/2011 የአዲስ አበባን ሁለቱ ዝነኛ ክለቦች ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ኢትዮጵያ ቡናን ያገናኘው የእግርኳስ ግጥሚያ ያለግብ ተጠናቀቀ።

የአብዛኛውን የእግርኳስ ቤተሰብ ቀልብ ስቦ የነበረውና ብርቱ ፉክክር ይደረግበታል የሚል ግምትን ያጫረው 'የሸገር ደርቢ' የተጠበቀውን ያህል ሳይሆን ያለውጤት ተጠናቅቋል።

በ52ኛው ደቂቃ የቅዱስ ጊዮርጊሱ ግብ ጠባቂ ፓትሪክ ማታሲ በኢትዮጵያ ቡናው አቡበከር ነስሩ ላይ በፈጸመው ጥፋት በቀይ ካርድ ወጥቷል።

የአዲስ አበባ ስታዲየም ያስተናገደው የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ ያለግብ መጠናቀቁን ተከትሎ ኢትዮጵያ ቡና የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ መሪ መሆን ችሏል፡፡

ሁለቱ ቡድኖች ከ1991 ዓም የውድድር ዘመን ጀምሮ 39 ጊዜ የተገናኙ ሲሆን ቅዱስ ጊዮርጊስ 18 ፤ ኢትዮጵያ ቡና ደግሞ ስድስት ጊዜ ድል ቀንቷቸዋል። በ15 ግጥሚያዎች ደግሞ ጨዋታቸውን በአቻ ውጤት አጠናቅቀዋል።

73 ግቦች በተስተናገዱባቸው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታዎች ቅዱስ ጊዮርጊስ 49 ኢትዮጵያ ቡና ደግሞ 24 ጊዜ ኳስን ከመረብ አገናኝተዋል።

በአዲስ አበባ ስታዲየም በተደረገው የዛሬው ጨዋታ የሰላም እና የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትሮች የተገኙ ሲሆን ደጋፊዎችም ጨዋታው በሰላም እንዲጠናቀቅ መልዕክት አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም