በኢትዮጵያ እየተከሰቱ ያሉ ችግሮች የፍትህ ስርአቱን ማጠናከር እንደሚገባ አመላካች ናቸው-ጠቅላይ ፍርድ ቤት

91

አዲስ አበባ ታህሳስ 21/2011 በኢትዮጵያ እየተከሰቱ ያሉ ችግሮች "የፍትህ ስርአቱን ማጠናከር የሚያስፈልግበት ጊዜ መሆኑን የሚያመለካቱ ናቸው" ሲሉ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ወይዘሮ መዓዛ አሸናፊ ተናገሩ።

ፕሬዚዳንቷ ይህን ያሉት የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ጉባኤ ሦስተኛ ዓመታዊ ስብሰባውን ዛሬ ሲያካሂድ ነው።

ወይዘሮ መዓዛ እንደተናገሩት፤ በአሁኑ ወቅት ህዝቡ በፍርድ ቤቶች ላይ ያለው እምነት እየቀነሰ መምጣቱ ተስተውሏል።

ለዚህም ደግሞ ስለዳኝነት ነጻነትና ገለልተኛነት በመንግስት ሃላፊዎችም ሆነ በህብረተሰቡ ዘንድ በቂ ግንዛቤ ያለመያዝና ዳኞች ተጠያቂ የሚሆኑበት ግልጽ መመዘኛ ያለመኖር እንደምክንያት ተጠቃሾች ናቸው።

በኢትዮጵያ ውሰጥ የህግ የበላይነትን መጣስ፣ የዳኝነት ስርዓቱ ውስጥ ጣልቃ መግባትና ፍትህ መጓደል እየተስተዋሉ ካሉ ችግሮች ውስጥ ይጠቀሳሉ።

ይህንን በመረዳት መንግስት ለዳኝነት ዘርፍ ከወትሮው የተለየ ትኩረት መስጠቱን ያወሱት ፕሬዚዳንቷ፤ ይህን መልካም አጋጣሚ በመጠቀም የፍርድ ቤት አመራር አባላት፣ ዳኞችና ሌሎችም ኃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባ አመልክተዋል።

የክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንቶች በክልላቸው በዳኝነት ስርአቱ ላይ እያጋጠሙ ያሉ ችግሮችና እየተሰሩ ያሉ ተግባራትን አቅርበዋል።

የጋምቤላ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ኦባንግ ኡጅሉ በክልሉ ነጻና ገለልተኛ የዳኝነት ስርአት እንዳልነበር በማንሳት "ለማስተካከል እየተሰራ ነው" ብለዋል።

የዳኞችን ብቃት ለማሳደግ የዜጎችን እንግልትና ቅሬታን ለመቀነስም በክልሉ ትኩረት የተደረገባቸው ነጥቦች ናቸው።

የሶማሌ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አቶ አብዱላሒ ሰኢድ፤ ቀደም ሲል በፍትህ ስርአቱ ላይ ጣልቃ ገብነት ይስተዋልበት እንደነበር አውሰተው፤ አዲስ የማደራጀት ተግባር እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።

የኦሮሚያ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ደሳ ቡልቻ  በበኩላቸው፤ የፍትህ ስርዓቱን ለማሻሻልና የህዘቡን ጥያቄ ለመመለስ አዲስ የማሻሻያ ስራዎች ተሰርቶ ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

የትግራይ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ዶክተር ፋና ሃጎስ እንዳሉት ክልሉ የፍትህ ስርዓቱን ለማዘመን አሰራሩን በቴክኖሎጂ ለመደገፍ ተግባራዊ እንቀስቃሴ እያካሄደ ነው። እንደ አገርም የፍትህ ስርዓቱን ለማዘመን ወጥ የሆነ የቴክኖሎጂ አሰራር የመዘርጋትን አስፈላጊነት አጽንኦት ሰጠውታል።

ፕሬዚዳንቷ ወይዘሮ መዓዛ አሸናፊ፤ በፍትህ ስርዓቱ ውስጥ ነጻነት፣ ተዓማኒነት፣ ግልጸኝነት እንዲሁም በቴክኖሎጂ መደገፍ በትኩረት የሚሰራባቸው ነጥቦች መሆናቸውን አብራርተዋል።

የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ጉባኤ የፌዴራል ፍርድ ቤት አመራር አባላትን፣ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኞችንና የሁሉንም ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንቶችን በአባልነት የያዘ ነው።

ጉባኤው በዓመት አንድ ጊዜ መካሄድ እንዳለበት በህግ ቢቀመጥም ባለፉት 27 ዓመታት የተካሄደው ሁለት ጊዜ ብቻ መሆኑ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም