በተፈጠሩ የኢንቨስትመንት አማራጮች ተጠቃሚ ሆነል-- የፍቼ ከተማ ባለሀብቶችና ነዋሪዎች

89
ፍቼ ግንቦት 17/2010 ባለፉት ዓመታት የተፈጠሩ የኢንቨስትመንት አማራጮች የአካባቢያቸውን ልማትና እድገት ከማፋጠን ባለፈ ኑሯቸው እንዲሻሻል ማድረጉን የፍቼ ከተማ  ነዋሪዎች ገለጹ። ከተማ አስተዳደሩ በበኩሉ የነጻ ኢኮኖሚ ስርዓት በከተማው ተግበራዊ ከሆነ ወዲህ ከ300 ሚሊዮን ብር በላይ ካፒታል ያላቸው የግል ባለሃብቶች በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች ለመሰማራት መቻላቸውን አስታውቋል ። ከከተማው ባለሃብቶች መካከል የቢፍቱ ቴክኒክ ትምህርት ኮሌጅ ባለቤት አቶ ተካ አንቸቤ እንዳሉት ከግንቦት 20 ድል በኋላ በአገሪቱ አዳዲስ ፖሊሲዎችና መመሪያዎች በመውጣታቸው በከተማው እርሳቸውን ጨምሮ ለበርካታ ባለሃብቶችና ነዋሪዎች ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል ። ለኢንቨስትመንት በተፈጠረው ምቹ ሁኔታ በግላቸው የቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ በመክፈት የከተማዋን ወጣቶች በተለያየ ሙያ በማሰልጠን ላይ መሆናቸውን የገለጹት አቶ ተካ፣ ከዚህ ጎን ለጎን  እራሳቸውም ተጠቃሚ እየሆኑ መምጣታቸውን ገልጸዋል። በአሁኑ ወቅት የከተማውን እድገት በሚመጥን መልኩ በ12 ሚሊዮን ብር ወጪ ሕንጻ  በማስገንባት ላይ መሆናቸውን ገልጸው ይህም ባለፉት 27 ዓመታት በኢንቨስትመንት ዘርፍ በአገሪቱ የተፈጠረው ምቹ ሁኔታ ውጤት መሆኑን ተናግረዋል። በሆቴልና ቱሪዝም ሥራ የተሰማሩት አቶ አብነት ፉፋ በበኩላቸው በ250 ሺህ ብር የጀመሩት የሆቴል ሥራ በአሁኑ ወቅት ካፒታሉን ወደ ሰባት ሚሊዮን ብር ማሳደጋቸውን ገልጸዋል። ባለፉት ዓመታት በመንግስት በተፈጠሩ ምቹ ሁኔታዎች በግላቸው የከተማው ዕድገት ተሳታፊና ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸው ይህም የድሉ ውጤት አንድ ማሳያ መሆኑን ነው የገለጹት። በሆቴል ሥራቸው ለ100 ሰዎች የሥራ ዕድል መፍጠራቸውን ጠቆሙት አቶ አብነት ዛሬ ለደረሱብት ደረጃ መሰረት የሆነውን የድል በዓል ሲዘክሩ ደስታ እንደሚሰማቸው ተናግረዋል። ባለፉት ዓመታት ዜጎች ያለገደብ ሀብት የማፍራት መብታቸው መረጋገጡ እርሳቻውን ጨምሮ በርካታ ባለሀብቶች ሰርተው እንዲለወጡ አድርጓል ብለዋል ። "በከተማው ከ27 ዓመት ወዲህ  የተፈጠሩት የንግድና የኢንቨስትመንት አማራጮች የሥራ አጥ ቁጥር እንዲቀንስ የበኩሉን አስተዋጽኦ ከማድረግ ባለፈ የዜጎች ኑሮ እንዲሻሻል ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል" ያሉት ደግሞ መምህር አልማዝ ደቻሳ ናቸው። በእዚህም በከተማው በግል ባለሀብት በተከፈተ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተቀጥረው ኑሯቸውን ለመምራት መቻላቸውን በማሳያነት ጠቅሰዋል። ባለፉት ዓመታት የተገኙ ውጤቶችና የነበሩ ችግሮችን በጥልቅ ተሀድሶ በመለየት የማስተካከያ ሥራዎች እየተሰሩ በላበት በአሁኑ ወቅት በዓሉ መከበሩ ልዩ እንደሚያደርገው ተናግረዋል። በግንቦት 20 ድል የሕዝቦች እኩልነት መከበሩንና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መስፈኑን የገለፁት ደግሞ በከተማዋ የመንግስት ሰራተኛው አቶ ሙሀመድ ጉዬ ናቸው። በጥልቅ ተሀድሶ የሕዝብ የመልካም አስተዳደርና የልማት ጥያቄዎች እንዲመለሱ መንግስት የሰጠውን ትኩረት እንደሚያደንቁም ገልፀዋል። የፍቼ ከተማ ምክትል ከንቲባ አቶ አለማየሁ እሸቱ በበኩላቸው  ባለፉት 27 ዓመታት በኢንቨስትመንት የተሰማሩ የግል ባለሀብቶች ከራሳቸው ባለፈ የአካባቢውን ማህበረሰብ ተጠቃሚ ሲያደርጉ መቆየታቸውን ተናግረዋል። በእነዚህ ዓመታት የከተማ አስተዳደሩ የባለሀብቶቹን ተሳትፎ ለማበረታታት ባደረገው ጥረት 333 ባለሀብቶችና አክሲዮን ማህበራት በኢንዱስትሪ፣ በማህበራዊ አገልግሎት፣ በሆቴልና ቱሪዝም እንዲሁም በአነስተኛና ከፍተኛ የንግድ ተቋማት ተሰማርተው ሥራ መጀመራቸውንም አስረድተዋል። እንደምክትል ከንቲባው ገለጻ፣ በባለሀብቶች የተገነቡ የጤናና የትምህርት ተቋማት ከ20 ሺህ የሚበልጡ የከተማዋ ነዋሪዎችን በቀጥታ ተጠቃሚ አድርገዋል። በከተማው  በ1986 ዓ.ም የዲዝል ጄነሬተር ወደ ኃይድሮኤሌትሪክ ኃይል እንዲቀየር መደረጉ የከተማዋን ነዋሪዎች ተጠቃሚ ከማድረጉ ባለፈ ባለሀብቶች የተሻለ የኃይል አማራጭ እንዲያገኙ እድል መፍጠሩንና ይህም በድሉ የተገኘ ውጤት መሆኑን አስረድተዋል። በላፉት ዓመታት በከተማዋ ለኢንቨስትመንት በተፈጠረው ምቹ ሁኔታም በአሁኑ ወቅት ከተማዋ የአራት ኮሌጆችና የአንድ ዩኒቨርሲቲ ባለቤት ነው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም