የወላጆችና ትምህርት ቤቶች ግንኙነት ዝቅተኛ መሆን ለተማሪዎች ስነምግባር ጉድለት አንዱ ምክንያት ነው ተባለ - ኢዜአ አማርኛ
የወላጆችና ትምህርት ቤቶች ግንኙነት ዝቅተኛ መሆን ለተማሪዎች ስነምግባር ጉድለት አንዱ ምክንያት ነው ተባለ
ታህሳስ 20/2011 በመዲናዋ የወላጆችና ትምህርት ቤቶች ግንኙነት ዝቅተኛ መሆን በተማሪዎች ላይ የሚስተዋሉ የስነ ምግባር ችግሮች በቂ መፍትሄ እንዳያገኙ ማድረጉን አንዳንድ የአዲስ አበባ የትምህርት ቤት ማህበረሰብና ተማሪዎች የተናገሩት፡፡
በመዲኃኒአለም መሰናዶ ትምህርት ቤት የ12ኛ ክፍል ተማሪ አብዱልራህማን አሊ በሰጠው አስተያየት ወላጆች እኛን አድገዋል፣ አዋቂ ናቸው በሚል ከትምህርት ቤቱ ጋር ያላቸው ግንኙነት አናሳ በመሆኑና ሁለቱም በጥምረት ክትትል ባለማድረጋቸው የሚታዩ የስነምግባራ ችግሮች በወቅቱ እንዳይታረሙ እያደረገ ነው ብሏል፡፡
ከስነምግባር ባሻገርም ተማሪዎቹ የሚጠበቅባቸውን ውጤት እንዳያስመዘግቡ ጫና አለው ያለው ተማሪ አብዱልራህማን ትምህርት ቤቶች ትውልድን በመልካም ስነምግባርና በእውቀት ለማነጽ ችግሩን መቅረፍ እንዳለባቸው ነው የተናገረው፡፡
የዚሁ ትምህርት ቤት የተማሪዎች ካውንስል ተማሪ ራሚስ ሰብስብ በበኩሏ በትምህርት ቤቱ የተማሪዎች ካውንስል ቢኖርም ለስም ከመቋቋም ውጭ በተማሪዎች ስነ ምግባር ላይ እየሰራ አይደለም ብላለች፡፡
"በሀገራችን ብቁ ዜጋን ማፍራት ያልተቻለበት ችግር ሁለተኛ ደረጃ ላይ ከደረስን መሯሯጥ ሳይሆን የሚያስፈልገው፣ ከስር ጀምሮ መንግስት መምህራንና ወላጆች መሰረት አስይዞ መምጣት ባለመቻሉ" ነው ያለችው፡፡
ሌላው የዚሁ ትምህርት ቤት የ12ኛ ክፍል ተማሪ አማኑኤል አጥናፉ ልጆች ወደ ትምህርት ቤት ከሚገቡበት ጊዜ ጀምሮ ቁሳቁስን ከሟሟላት ባሻገር የቅርብ ክትትልና ድጋፍ ማድረግ ወሳኝ መሆኑን ተረድተው የሚሰሩ ወላጆች ውስን እንደሆኑ ይናገራል፡፡
ተማሪ አማኑኤል ከቤተሰቡ ጋር በሰፊው የመገናኘት እድል ባይኖረውም እራሱን ከአልባሌ ቦታ በማራቅ በመልካም ስነምግባር ትምህርቱን በመከታተል ጥሩ ውጤት እያስመዘገበ መሆኑን ገልጿል፡፡
“እኔ ማንነቴንና ወዴት እንደምሄድ ህልሜን ካወቅኩኝ አላስፈላጊ ነገሮች አይደለም በትምህርት ቤት አከባቢ ይቅርና በመማሪያ ክፍልም ብገኝ አላማዬን ነው እንጂ ተጽኖ ያሳድርብኛል ብዬ አላምንም፤ ስለሆነም የቤተሰብና የሀገር አደራ ስላለብን በመጤ ባህል ሳንታለል ጠንክረን መውጣት አለብን’’ ብላል፡፡
በቀጣይ ወደ ከፍተኛ የትምህርት ተቋም ስገባም ሰላምን በማስጠበቅ ና ለስኬት ለመብቃት ከጓደኞቹ ጋር በእውቀት በመመራትና ምክንያታዊ በመሆን የግጭት መነሻ የሆኑ ጉዳዮችን በተረጋጋ መንፈስ በመፍታት የበኩሉን ለማበርከት ከአሁኑ ዝግጁ መሆኑን ይናገራል፡፡
የመድኃኒአለም ትምሀርት ቤት የ12ኛ ክፍል ተማሪና የተማሪዎች ተወካይ ተማሪ ጽዮን ጨዋቃ በበኩሏ ወላጆች ከትምርት ቤት ጋር ባለመስራታቸው ባለፈው አመት “መቆጣጠር አልቻልንም አቃተን” ተብሎ መመለስ የማይቻል ደረጃ ላይ ስደርሱ የሚመጡ ወላጆች መኖራቸውን ታስታውሳለች፡፡
ትምህርት ቤቱም አስቀድሞ ከወላጅ ጋር ጥብቅ ግንኙነት ሳያደርግ በስነምግባር ችግር ያባረራቸው ብዙ ተማሪዎች እንደነበሩና በአልባሌ ቦታዎች እየዋሉ መሆናቸውንም ትጠቅሳለች፡፡
አንዳንድ ተማሪዎች ወላጅ አምጡ ስባሉ ወላጄ ነው ብለው የሚያመጡትን ትምህርት ቤቱ ወላጅ ስለመሆናቸው ሳያጣራ በመቀበሉ ወላጅ ያልሆኑት እንደ ወላጅ ሆነው ስለሚመጡ የስነምግባር ችግሩ እንዳይፈታ አንዱ ምክንያት ሆኗል ብላለች፡፡
’’ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ቀደም ሲል ለተማሪዎች የውጭ ትምህርት እድል መስጠታቸው ለእኔ ከፍተኛ ተስፋና ተነሳሽነት ስለፈጠረብኝ እድሉን ለማገኘት በጉጉት እየተማርኩ ነው’’ ብላለች፡፡
በመሰናዶ ትምህርት ቤቱ ምክትል ርዕሰ መምህር ዱጋሳ ፈቃዱ በበኩላቸው የወላጅ፣የትምህርት ቤትና የተማሪ ግንኙነት አናሳ መሆኑ በተማሪዎች ውጤትና ስነምግባር ላይ ከፍተኛ ችግር እየፈጠረ እንደሆነ ገልጸው ችግሩን ለመፍታት በዚህ ዓመት በትኩረት ለመሥራት ገና በዝግጅት ላይ እንደሆኑ ይናገራሉ፡፡
በዚህ ትምህርት ቤት የወላጅ ተሳትፎ አነስተኛ እንደሆነ የሚናገሩት የኮሚቴ አባል አቶ ጌራወርቅ ገዝቡ፤ ለዚህ ዋናው ምክንያት አንዳንድ ወላጆች ልጆቻቸው በእድሜና በትምህርት ደረጃ ከፍ እያሉ ስሄዱ ራሳቸውን ችለዋል በማለትና የትምህርት ስራን ለመምህራን ብቻ የመተው አስተሳሰብ ነው ብለዋል፡፡
ባለፈው የትምህርት ዘመን ወላጆች ከትምህርት ቤቱ ጋር በጥምረት ባለመስራታቸው የተማሪዎች ውጤት ዝቅተኛ እንደነበር ያነሱት አቶ ጌራወርቅ በዚህ ዓመት በጋራ ለመሥራት በአዲስ መልክ ተወያይተው የተማሪዎችን ውጤትና ስነምግባር ለማሻሻል ወደ ስራ መግባታቸውንም ገልጸዋል፡፡
በተለያዩ ትምህርት ቤቶች ላይ ለረጅም ጊዜ በወላጅ ኮሚቴነት የሰሩና በአሁኑ ጊዜ በኒው ኤራ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የወላጅ ኮሚቴ ሰብሳቢ ሆነው እያገለገሉ እንደሆነ የተናገሩት አቶ በድሩ ሁሴን እንዳሉት የወላጅ ኮሚቴ በትክክል ከሰራ ከትምህርት ቤቱ አስተዳደርና መምህራን በበለጠ ለተማሪዎች ሰፊ እገዛ ማድረግ ይቻላል፡፡
እስካሁን በነበራቸው ልምድም ወላጅና ትምህርት ቤት በጋራ ሃላፊነታቸውን በአግባቡ ባመለወጣታቸው እየታየ ያለው የትምህርት ጥራት ማነስ፣ የስነ ምግባር ና የሰላም ችግር አሳሳቢ ደረጃ ላይ እንዲደርስ ምክንያት ሆኗልም ነው ያሉት፡፡
የትምህርት ቤቱ የወላጅ ኮሚቴ ከአንደኛ ክፍል ተማሪ ጀምሮ በስነምግባራቸው፣ በትምህርት አቀባበላቸው፤ በውሎአቸው፣ በአለባበስና ጸጉር አቆራረጣቸው እንዲሁም መጤ ባህልን ከመከላከል አንጻር የተሻለ ትውልድን ለማፍራት በየቀኑ በትምህርት ቤቱ በመገኘት ክትትል እያደረጉ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡
በእለታዊ ኑሮ በመጠመድ ብቻ ሳይሆን ልጃቸውን ወደ ትምህርት ቤት መላኩ ብቻ እንደማስተማር የሚቆጥሩ ወላጆች መኖራቸውን የገለጹት አቶ በድሩ አሁን እየታየ ያለው ተሳትፎ መልካም እንደሆነ ይናራሉ፡፡
“ከመሰረቱ ካልተያዘ ቦኃላ ሲያድጉ መመለስ አይቻልም” ያሉት ሰብሳቢው ታዳጊዎችን ከስሩ ኮትኩቶ ስነምግባር የተላበሰ ሀገር ወዳድ ዜጋን ለማፍራት ለተወሰነ አካል የሚታው ሳይሆን ሁሉም ዜጋ ርብርብ ማድረግ አለበትም’’ ብለዋል፡፡
በመድኃኒያለም መሰናዶ ትምህርት ቤት የስነ ዜጋና ስነምግባር መምህር ስለሺ እሸቱ በበኩላቸው ተማሪዎች ከ5ኛ ክፍል ጀምሮ እስከ ከፍተኛ ትምህርት ተቋም ድረስ የስነዜጋና ስነምግባር ትምህርት ብማሩም የባህሪ ለውጥ እየመጣ እንዳልሆነ ይናገራሉ፡፡
በዚህ ጉዳይ ላይ በአንዳንድ የአዲስ አበባ ትምህርት ቤቶች የችግሩን መንስኤ ጥናት እንዳደረጉ የተናገሩት መምህር ስለሺ ከተማሪዎች ያገኙት ውጤት “ዕኛ በክፍል የሚንማረውና በውጭ ደግሞ በተግባር የሚናገኘው ተቃሪኒ ሆኖ በመገኘቱ ከቤተሰብ፣ ከአከባቢና ከትምህርት ቤት የሚናገኘነው ነው የምንከተለው” የሚል እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
የተማሪዎች ቤተሰብም “ለትምህርት የሚሰጠው ቦታ አናሳነው፤ እንደ ማሳያም የመምህሩን ይህወት ስናይ የተጎሳቆለ ነው፣ ስለዚህ መንግስት ለትምህርት ቦታ እየሰጠ አደለም” የሚል ምላሽ እንዳኙ ተናግረዋል፡፡
ከመምህራን ደግሞ “ህይወትን ለማሸነፍ መሯሯጥ” ተደማምረው የተማሪን ውጤትም ሆነ ስነምግባር ላይ ችግር ፈጥሯል የሚል የጥናት ውጤት አግኝቻለው ብለዋል፡፡
ትምህርት የሁሉም መነሻ በመሆኑ ውጤታማ፣ በስነምግባር የተመሰገነና ሀገር ተረካቢ ዜጋን ለማብቃት ወላጅ፣ የትምህርት ቤትና የአከባቢው ማህበረሰብ በቅርበት መስራት ወሳኝ ቢሆንም መንግስትም ልዩ ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንደሚገባው መምህር ስለሺ ምክር ለግሰዋል፡፡