የበለፀገችና አንድነቷ የተጠናከረ አፍሪካ ለመፍጠር በቅድሚያ ሙስናን መከላከል ይገባል-ሙሳ ፋቂ ማሃማት

57
አዲስ አበባ ግንቦት 17/2010 የበለፀገችና አንድነቷ የተጠናከረ አፍሪካን ለመፍጠር በቅድሚያ ሙስናን መከላከል እንደሚገባ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋቂ ማሃማት ገለፁ። 55ኛው የአፍሪካ ቀን የተከበረው የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን ለመሰረቱ ቀደምት መሪዎች ክብር በመስጠት ነው። እለቱ “ለአፍሪካ ለውጥ ከሙስና ጋር የሚደረገውን ትግል ማሸነፍ'' በሚል መሪ ሐሳብ በአፍሪካ ህብረት አዳራሽ ተከብሯል። የህብረቱ ኮሚሽነር ሙሳ ፋቂ ማሃማት የቀድሞው የአፍሪካ አንድነት ደርጅት መመስረት አገራትን ከቅኝ ግዛት በማላቀቅ እና አሁን ላለችውና ወደፊት እንድትሆን ለምንፈልጋት አፍሪካ መነሻ እንደነበር ገልፀዋል። በዚህ ዓመት የአፍሪካ ነፃ የአየር ትራንስፖርት ገበያ ስምምነት እና የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጠና ስምምነት መፈረሙ የህብረቱና የአፍሪካውያን ስኬት መሆኑን ገልፀዋል። ይሁን እንጂ አሁንም የምንፈልጋትን አፍሪካ ለመፍጠር ፈተና የሚሆነው ሙስና መሆኑን ጠቅሰዋል። ሙስና በዜጎችና በሀገራት ላይ የሚያደርሰውን ተፅዕኖ በመረዳት ሁሉም ኃላፊነቱን ለመወጣት የሚደረገውን ትግል ማጠናከር ይገበዋል ብለዋል። በርካታ የአፍሪከ ሀገራት በዓለም ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት ካላቸው ሀገራት ተርታ መሰለፋቸው ተስፋ መሆኑን ገልፀው፤ ይህን ለማስቀጠል ግን የአየር ንብረት ለውጥን መከላከል፣ የምግብ ዋስትና ማረጋገጥ እና ኢንዱስትሪ ማስፋፋት የወደፊት ትኩረት ሊሆኑ ይገባል ብለዋል። በአፍሪካ ህብረት የናይጄሪያ ቋሚ ተወካይ ሚስተር ባንኮሌ አዲዎየ የዘንድሮውን የሙስና መከላከል አምባሳደር ፕሬዝዳንት ማህሙዱ ቡሃሪን ወክለው መልዕክት አስተላልፈዋል። ተወካዩ በንግግራቸው አፍሪካ ያላትን ሀብት መጠቀም ያልቻለችው ሙስና በፈጠረው ውሰብስብ ችግር መሆኑን ጠቅሰዋል። "አፍሪካውያን ቅኝ ግዛትን እንዳስወገዱ ሁሉ ሙስናንም ማሸነፍ ይችላሉ፤ ለዚህም ሁሉም የማህበረሰብ ክፍል ተዋናይ መሆን አለበት" ብለዋል። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ሂሩት ዘመነ በበኩላቸው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ሲመሰረት ዓላማው ፓን አፍሪካኒዝምን ማራመድ ነበር፤ ዓላማውንም አሳክቷል ብለዋል። ይህን ለአንድነታችን መሰረት የሆነውን ታሪካዊ ቀን ስናከብር ደግሞ ከሙስና ጋር የሚደረገውን ትግል በማጠናከር መሆን እንዳለበት ገልፀዋል። ኢትዮጵያ አፍሪካውያን ሙስናን ለመታገል የሚያደርጉትን ትግል ለመደገፍ ዝግጁ መሆኗን ገልፀው መንግስት  ከሁሉም ማህበረሰብ ጋር በመሆን ይሰራል ብለዋል። የአፍሪካ አንድነት ድርጅት እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ1963 በቀዳማዊ ኃይለ ስላሴ፣ በጋናዊው ክዋሜ ንኩሩማህ፣ በግብፁ ገማል አብዱል ናስር፣ በታንዛኒያው ጁሊዬስ ኔሬሬ እና በጊኒው አህመድ ሴኮቱሬ አማካኝነት መመስረቱ ይታወሳል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም