በስድስተኛው የኢትዮጵያ ወጣቶች አትሌቲክስ ሻምፒዮና ሰባት የፍጻሜ ውድድሮች ተካሄደዋል

አሰላ  ግንቦት 17/2010 በስድስተኛው የኢትዮጵያ ወጣቶች አትሌቲክስ ሻምፒዮና በዛሬ ውሎው ሰባት የፍጻሜ ውድድሮች ተካሄደዋል። በሻምፒዮናው የዛሬው ሶስተኛ ቀን ውሎው  በሁለቱም ጾታ የ800 ሜትርና የ400 ሜትር ውድድሮች ፍጻሜቸውን አግኝተዋል። በወንዶች የ800 ሜትር  ውድድር ታደሰ ለሚ ከኦሮሚያ አንደኛ  ሆኖ አጠናቋል። ለአፍሪካ ኦሎምፒክ ቡድን የተመረጠውና ያለውን አቅም ለመፈተሽ የተወዳደረው ጣሰው ያዳ ሁለተኛ ሆኖ ሲያጠናቅቅ አዲሱ ግርማ ከኦሮሚያ ውሃ ስራዎች ሶስተኛ ደረጃን ይዞ አጠናቋል። በሴቶች የ800 ሜትር ድርቤ ወልተጂ ከኦሮሚያ አንደኛ ሆና አጠናቃለች። የሲዳማ ቡናዋ አትሌት ሂሩት መንገሻ  ሁለተኛ ሆና ስታጠናቅቅ  ፍሬወይን ኃይሉ ከመስፍን ኢንዱስትሪያል ሶስተኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች። በሴቶች የ400 ሜትር ውድድር በድንቅ አጨራረስ አንደኛ ሆና ያጠናቀቀችው የኢትዮጵያ ንግድ ባንኳ አትሌት ፍሬሂወት ወንዴ ናት። የክለብ አጋሯ  ማህሌት ፍቅሬ ሁለተኛ ደረጃን ይዛ ስታጠናቅቅ  የኦሮሚያዋ ፍሬዘውድ ተስፋዬ ሶስተኛ ወጥታለች። በዛሬው እለት ፍጻሜያቸውን ካገኙ ስፖርቶች መካከል የወንዶች ስሉስ ዝላይ፣ የአሎሎ ውርወራና የሴቶች የርዝመት ዝላይ ይገኙበታል። በእለቱ የ5 ሺህ ሜትር የወንዶች ሩጫን ጨምሮ በሰባት ስፖርቶች የማጣሪያ ውድድሮች ተካሄደዋል። ውድድሩ ነገ ቀጥሎ ሲውል የፕሮግራም ሽግሽግ የተደረገበት የሴቶች 5 ሺህ ሜትር ሩጫ ፍጻሜ ይደረጋል። እንዲሁም በሁለቱም ጾታ የ10 ሺህ ሜትር የእርምጃ ውድድርና ሌሎች የፍጻሜና የማጣሪያ ውድድሮች ይደረጋሉ። በርካታ የአሰላና አካባቢዋ ነዋሪዎች ውድድሩ በሚካሄድበት የአሰላ አረንጓዴው ስታዲየም በመገኘት ለአትሌቶቹ ሞራል በመስጠት የውድድሩ ትልቅ  ድምቀት እንደሆኑ ቀጥለዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም