ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ የጀመረችው ተግባራዊ የለውጥ እንቅስቃሴ በለጋሾች ዘንድ እምነት እንዲጣልበት እያደረገ ነው - ምሁራን

አዲስ አበባ ታህሳስ 20/2011ኢትዮጵያ በኢኮኖሚና በፖለቲካው ዘርፎች እያሳየችው ያለው ተግባራዊ የለውጥ እንቅስቃሴ በአለማቀፍ ለጋሽ አገሮች ዘንድ ብድር የመክፈል አቅሟ እምነት እንዲጣልበት ማድረጉን የምጣኔ ሃብት ምሁራን ተናገሩ።

በተጠናቀቀው የፈረንጆቹ ዓመት የዓለም ባንክ ለኢትዮጵያ የ1 ነጥብ 35 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ብድርና ድጋፍ ሰጥቷል።

ይህም ባንኩ ከዚህ ቀደም ከሚያደርገው ድጋፍ ከሶስት እጥፍ በላይ ጭማሪ ማሳየቱን ያመለክታል።

የአፍሪካ ልማት ባንክ ፣ የአውሮፓ ህብረትና ሌሎች አገሮችም ድጋፍ በማድረግ ላይ መሆናቸውን መረጃዎች ይጠቁማሉ።

በቅርቡ በአገሪቷ በተከሰተው የለውጥ ሂደት የተጀመሩ ተግባራዊ እንቅስቃሴዎች ዓለም አቀፍ ትኩረት መሳቧን በተለያየ መልኩ ሲገለጽ ይታያል።

ለአብነት ባለፈው ዓመት መጨረሻ  በመንግስት ይዞታ ሥር ያሉ የባቡር፣ የስኳር ልማት፣ የኢንዱስትሪ ፓርክ፣ የሆቴል እና የተለያዩ የማኑፋክቸሪንግ ድርጅቶች ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል በአክሲዮን ሽያጭ ወደ ግል ዘርፍ እንዲተላለፉ መወሰኑ የተሰጠውን ትኩረት መጥቀስ ይቻላል።

የኢትዮ-ቴሌኮም፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫዎች እና የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ድርጅት ትልቁን የአክሲዮን ድርሻ መንግስት ይዞ ቀሪው ለአገር ውስጥ እና ለውጭ ባለሃብቶች በአክሲዮን ድርሻ እንዲተላለፉ አቅጣጫ መቀመጡም ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በጉዳዩ ዙሪያ ያነጋጋራቸው የምጣኔ ሀብት ምሁራን እንደሚሉት፤ የዚህ ዓይነቱ በተግባር የተደገፈ የለውጥ እንቅሰቃሴ ለአገሪቷ አጋር የሆኑ ድጋፍ ሰጪ ተቋማትን ቀለብ ገዝቷል።

የምጣኔ ሃብት ምሁሩ ዶክተር ብርሃኑ ደኑ እንደሚሉት፤ አሁን እየታየ ያለው ለውጥ በአለማቀፍ ለጋሽ አገሮች ዘንድ ብድር የመክፈል አቅም እምነት እንዲጣልበት አድርጓል።

የውጭ አገራት ድጋፍ ሰጪዎች አጠቃላይ የገንዘብ ድርጅቶች የገንዘብ ስርጭትና አጠቃቀም ብቻ ሳይሆን የፖለቲካውንም ስርዓት የሰብዓዊ መብት አያያዝንም ጉዳይ ይከታተላሉ ያሉት ምሁሩ በዚህ የተነሳ ኢትዮጵያ አሁን የያዘችው የለውጥ አቅጣጫ አወንታዊ የኢኮኖሚ እድገት ለማምጣት ያስችላል ብለዋል፡፡

ሌላኛው የምጣኔ ሃብት ምሁር ዶክተር ደሳለኝ ሻሚቦ እንደሚናገሩት፤ እየጨመረ የመጣውን የአገሮች የብድር ድጋፍ ለመመለስ አሁን የተጀመረውን ለውጥ ማስቀጠል ይገባል። በአገሪቷ ሰላም፣ መረጋጋትና የተያዙ የልማት እቅዶች ማፋጠን ላይ ትኩረት ሰጥቶ መሰራትም ያስፈልጋል።

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የአገሪቷ ብድር የመክፈል አቅም ተዳክሞ እንደነበር አለማቀፉ የገንዘብ ድርጅት አመላክቶ ነበር።

የአገሪቷ ዕዳ በአማካኝ 25 ነጥብ 5 በመቶ እየጨመረ ነው እ.አ.አ በ2008 ከነበረበት 2 ነጥብ 8 ቢሊዮን በ2017/18 ወደ 26 ነጥብ 4 ቢሊዮን ዶላር ማደጉን መረጃዎች ያመለክታሉ።

እነዚህ  ደግሞ አዋጭ ባልሆኑ ፕሮጀክቶች ላይ በርካታ ማዋዕለ ንዋይ ማፍሰስ፣ የፕሮጀክቶች በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ አለመጠናቀቅና የተመደቡ ገንዘቦች ለታለማላቸው ዓላማ አለማዋል ዋነኞቹ ናቸው።

አገሪቱ በኢኮኖሚና በፖለቲካው ዘርፎች እያሳየችው ያለው ተግባራዊ የለውጥ እንቅሰቃሴ እነዚህ ችግሮን በፍጥነት በመፍታት የተገኘውን እንደ መልካም አጋጣሚ መጠቀም ያስፈልጋል ብለዋል።

የምጣኔ ሃብት ባለሙያ ዶክተር ተስፋዮ ጫፎ በበኩላቸው በተወሰኑ ምርቶች ላይ ተንጠልጠሎ ያለውን የውጭ ገበያ ወደ በማብዛት እንደ ቆዳና ቆዳ ውጤቶች ፣ጥራጥሬና ሌሎች የቅባት እህሎች በጥራትና በስፋት በማምረትና ሌሎች አማራጭ ዘርፎችን መጠቀም ወሳኝ ነው ሲሉ ተናግረዋል።

የብድር የመክፈል አቅምን ለመጨመር የተቋማትን የቁጥጥር አቅም ማሳደግ ሌላኛው ብድርን የመክፍል አቅም የመጨመር አማራጭ መሆኑንም ነው ያመላከቱት።

አገራዊ አቅም መገንባትና ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በአገር ውስጥ የመተካቱ ስራ ሊጠናከር ይገባል።   

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም