የህግ የበላይነት እንዲከበር ተጠየቀ

77

ጎባ/አምቦ ታህሳስ 19/2011 በባሌ ዞን ራይቱ ወረዳ የደደቸ በልዓ ከተማ ነዋሪዎች የህግ የበላይነት እንዲከበር ትናንት ባካሄዱት ሰልፍ ጠየቁ፡፡

ነዋሪዎቹ  ሰልፉን ያደረጉት በአካባቢው የጨልጨል ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህር ከትናንት በስቲያ ሌሊት ማንነታቸው ባልታወቁ ሰዎች መገደላቸውን ተከትሎ ነው፡፡

በሰልፉ የተሳተፉት ወጣቶች፣ ሴቶች፤ የኃይማኖት አባቶችና ሌሎችም የከተማዋ  ነዋሪዎች "የህግ በላይነት ይከበር ፤ በየቦታው የሰውን ክቡር ህይወት የሚያጠፉ ተጠርጣሪ ወንጀለኞች በህግ ሊዳኙ ይገባል፤ የሰው ሞትና መፈናቀል ይቁም" የሚሉ መፈክሮች አሰምተዋል።

ከሰልፉ ተሳታፊዎች መካከል አቶ ጄይላን መሐመድ በሰጡት አስተያየት የተፈጸመው ተግባር ከኦሮሞ ህዝብ ማንነትና እሴት ያፈነገጠና አሰፋሪ ድርጊት ነው በማለት አውግዟል፡፡

በዚህ አስነዋሪ ድርጊት የተሳተፉ ተጠርጣሪዎች ታድነው ለህግ እንዲቀርቡም ጠይቀዋል፡፡

ወጣት ሁሴን ከማል በበኩሉ  የነገ ሀገር ተረካቢ ዜጋን የሚያፈራ መምህር ህይወቱ ማለፉ እንዳሰዘሰነው ተናግሮ መንግስት አጥፊዎቹን በአስቸኳይ ተከታትሎ በመያዝ  ለህግ እንዲቀርቡ ማድረግ እንዳለበት አመልክቷል፡፡

ነዋሪዎቹ መንግስት በሀገሪቱ የህግ የበላይነትን ለማስከበር እያደረገ ያለውን  ጥረት እንደሚደግፉ ገልፀዋል፡፡

የራይቱ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ መሐመድ አወል ከድር በበኩላቸው ሰላማዊ ሰልፉ የተካሄደው ለጊዜው ማንነታቸው ባልታወቁ ሰዎች  በተገደለው መምህር ህዝቡ በመቆጣቱ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የተካሄደው ሰልፍ ህጋዊና እውቅና ያለው መሆኑን ጠቅሰው በጉዳዩ ጋር የተጠረጠሩ ዘጠኝ ግለሰቦች ተይዘው  ምርመራ እየተደረገባቸው መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

አስተዳዳሪው እንዳሉት መንግስት ተጠርጣሪ ወንጀለኞችን አድኖ ለህግ ለማቅረብ የሚያደርገውን ጥረት ውጤታማ እንዲሆን የአካባቢው ማህበረሰብ ሊተባበረው እንደሚገባም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ በምዕራብ ሸዋ ዞን ደንዲ ወረዳ   ማንነታቸው ባልታወቁ ታጣቂዎች በተከፈተው ተኩስ አንድ ሰው ህይወት ሲልፍ በሁለት ሰዎች ላይ የአካል ጉዳት መድረሱን ፖሊስ አስታውቋል፡፡

የወረዳው ፖሊስ መምሪያ አዛዥ ዋና ኢንስፔክተር ይገዙ ገብረሚካኤል እንደገለጹት  ጥቃቱ የተፈጸመው  ትናንት ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት  አካባቢ ነው፡፡ 

ጥቃቱ የተፈጸመባቸው በዞኑ  የአካባቢ  ጥበቃና የአየር ለውጥ ባለስልጣን ሰራተኞች በተሽከርካሪ ከጀልዱ ወረዳ ከመስክ ስራ ሲመለሱ በደንዲ  ጭልሞ ጋጂ ልዩ ስሙ ማዞሪያ አስር  በተባለ ስፍራ ሲደርሱ በተተኮሰባቸው ጥይት እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

በአደጋው የአካል ጉዳት የደረሰባቸው በአምቦ ሪፈራል ሆስፒታል የህክምና እርዳታ እየተደረገላቸው መሆኑን ያመለከቱት አዛዡ የሟቹ አስክሬን አዲስ አበባ ምኒሊክ ሆስፒታል ለምርመራ  መላኩንና  ጥቃቱን የፈጸሙትን ለይቶ ለመያዝ ፖሊስ በክትትል ላይ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም