ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ ትረስት ፈንድ እስካሁን ከአንድ ሚሊዮን ዶላር በላይ ተሰበሰበ

አዲስ አበባ ታህሳስ 19/2011 በኢትዮጵያ ትረስት ፈንድ ሂሳብ ቁጥር ለዲያስፖራው ድጋሚ ጥሪ ከተደረገ በኋላ እስከ አሁን ከአንድ ሚሊዮን ዶላር በላይ ገንዘብ ተሰብስቧል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ማህበረሰብ የተሻለች ኢትዮጵያን ለመገንባት በሚደረገው እንቅስቃሴ የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ ጥሪ ማቅረባቸው ይታወሳል።

በዚሁ መሰረት የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ትረስት ፈንድ በንግድ ባንክ ሂሳብ ቁጥር ተከፍቶ አገልግሎት መስጠት መጀመሩ ይታወቃል።

ይሁንና በቅርቡ በትረስት ፈንዱ ሂሳብ ቁጥር በርካታ ዲያስፖራዎች አለመሳተፋቸውን ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ድጋሚ ጥሪ ማድረጋቸው ይታወሳል።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽህፈት ቤት ዛሬ ይፋ እንዳደረገው ጥሪውን ተከትሎ በርካታ ዲያስፖራዎች በመሳተፍ ከታቀደው ገንዘብ በላይ ተሰብስቧል።

ትረስት ፈንዱ እያንዳንዱ የኢትዮጵያ ዲያስፖራ በቀን አንድ ዶላርና እንደ አቅሙ ለአገሩ አስተዋጽኦ የሚያደርግበት አሰራር ሲሆን ለመሰብሰበ ከታቀደው አንድ ሚሊዮን ዶላር በላይ መሰብሰቡ ታውቋል።

የገንዘቡ ከታቀደው በላይ መሰብሰብ የዲያስፖራው ተሳትፎም በኢትዮጵያ አብሮነት ውስጥ ታላቅ ኃይል እንዳለ አሳይቷል ነው የተባለው።

በቀሩት ተጨማሪ ቀናትም በርካታ ገንዘብ ይሰበሳባል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን ገንዘቡ ለልዩ ልዩ የማህበራዊ አገልግሎትና የልማት ስራዎች ይውላል።

በአዲሱ የአውሮፓውያን 2019 ዓመትም በውጭ አገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን በዚሁ ልግስና እንዲቀጥሉ ጥሪ ቀርቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም