ቀጥታ፡

የባቢሌ ዝሆኖችን ከጥፋት ለመታደግ የተቀናጀ ስራ ያስፈልጋል ተባለ

ድሬዳዋ ታህሳስ 18/2011 የባቢሌ ዝሆኖች እየደረሰባቸው የሚገኘውን ጫናና የመጥፋት አደጋ ለመታደግ የተቀናጀ ስራ እንደሚያስፈልግ ተገለጸ፡፡

" እኔ ለተፈጥሮ ሃብት አምባሳደር ነኝ"  በሚል መሪ ሃሳብ በድሬዳዋ የባቢሌ ዝሆኖች መጠለያ  የተፈጥሮ ሃብትን ከጥፋት ለመከላከል በሚቻልበት ዙሪያ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችና አመራሮች ተወያይተዋል፡፡

በውይይቱ ወቅት እንደተገለጸው  መጠለያው በሚደርስበት ጫናና ጥፋት የተነሳ ዝሆኖቹ በአስጊ ሁኔታ ላይ ይገኛሉ፤ በሰው የሚገደሉ  ዝሆኖች ቁጥራቸው በርካታ  ነው፡፡

የመጠለያው ስካውት ሰብሳቢ አቶ አራርሶ አህመድ እንዳሉት  በዱር እንስሳቱ ላይ ሀገ-ወጥ አደን፣ ልቅ ግጦሽ፣  ሰፈራ፣  እርሻና ደን ጭፍጨፋ እንዲሁም የተፈጥሮ ማዕድን ማውጣት ይካሄዳል፡፡

"ችግሩን ለመከላከል ከህብረተሰቡ ጋር በመሆን የሚቻለውን ሥራ ብንሰራም የጠባቂዎቹ ቁጥር በጣም አነስተኛ በመሆኑ ውጤት አላመጣም፤ ችግሩን ለመፍታት ትኩረት ሊደረግበት ይገባል "ብለዋል፡፡

በመጠለያ አካባቢ የሚኖሩ የፈዲሶ ወረዳ አርሶ አደር ኡስማን መሐመድ በበኩላቸው የዝሆኖቹ መጠለያ ለችግር መዳረጉ ዝሆኑም ወደ መንደር በመግባት ጥፋት እያደረሰ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

" እኔ ያወኩትን ለህብረተሰቡ በማሳወቅ በቡድንም በመደራጀት የዝሆኑን መጠለያ መጠበቅ አለብን" ብለዋል፡፡

በመጠለያው እየደረሰ ያለው ህገ-ወጥ ደን ጭፍጨፋና ከሰል ማክሰል እየተባባሰ እንደሚገኝ ያመለከቱት ደግሞ በመጠለያው የቱሪዝም ባለሙያ አቶ ገዛኻኝ ፍቃዱ ናቸው፡፡

መጠለያው በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች ውስጥ የሚገኝ በመሆኑ ክልሎቹ  ተቀናጅተው በመስራት  የመሬት ሽሚያውን ማስቀረት እንደሚያስችል ተናግረዋል፡፡

አንደባለሙያው ገለፃ በመጠለያው አካባቢ ለሚገኙ ነዋሪዎች አማራጭ የሥራ ዕድል በመፍጠር የህዝቡን የመሠረተ ልማት ጥያቄዎች በመመለስ  ጭምር መጠለያውንና ዝሆኑን ለመታደግ መረባረብ ያስፈልጋል፡፡

በኦሮሚያ የአባገዳዎች ሰብሳቢ  አባገዳ በየነ ሰንበቶ በበኩላቸው በኦሮሞ የገዳ ባህል  የተፈጥሮ ሃብት ፣የዱር አራዊት፣ ዛፍና ቅጠል የሚጨፈጭፍ የተወገዘ ተግባር መሆኑ ገልጸዋል፡፡

በባህሉ መሠረት የሚበቅል እንጨትና የሚያድግ ልጅ ማጥፋት ፈፅሞ የተወገዘ መሆኑን ጠቁመው "ህብረተሰቡ ይህን በመረዳት ከዝሆኖቹ መጠለያ ራሱን መለየትና ለተፈጥሮ ሃብቱ ጥበቃ ሊያደርግ ይገባል "ብለዋል፡፡

ይህን የሀገር ሃብት ለመጠበቅ  ኃላፊነታቸውን እንደሚወጡ የተናገሩት አባገዳው የሰንቅሌ ቆርኪዎች ከጥፋት ለመታደግ አባገዳዎችና የጎሣ መሪዎች ያበረከቱትን የመሪነትና የባለቤትነት አስተዋጽኦ ዛሬም ዝሆኖቹን ከመጥፋት ለመታደግ መዋል እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡

የምሥራቅ ሐረርጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሁሴን ፈይሶ የፖለቲካ ቁርጠኝነት አለመኖሩ በመጠለያውና በዝሆኖች ላይ እየደረሰ የሚገኘውን ችግር ማቃለል አለመቻሉን ተናግረዋል፡፡

ህገ-ወጥ ሰፈራና በኢንቨስትመንት ስም የሚካሄድ የልማት እንቅስቃሴ መጠለያውን ለጉዳት እየዳረጉት መሆኑን ተናግረው "በቀጣይ በየደረጃው የሚገኙት የህብረተሰብ ክፍሎች ፣ የሀገር ሽማግሌዎች አባገዳዎች ጋር በመቀናጀት የተሻለ ውጤት የሚያመጣ ሥራ ይሰራል" ብለዋል፡፡

የሱማሌ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል  ኃላፊ ወይዘሮ ሂቦ አህመድ በበኩላቸው የተፈጥሮ ሃብቱና ዝሆኑ ለሁለቱ ተጎራባች ክልሎች ማህበራዊና ምጣኔ ሃብት ዕድገት ሁነኛ አስተዋጽኦ  ያለው ፀጋ በመሆኑ የተሻለ ቅንጅት በመፍጠር እንደሚሰሩ ተናግረዋል፡፡

ወይዘሮ ሂቦ እንዳሉት በመጠለያው አካባቢ የሚኖሩና በየደረጃው የሚገኝ ህብረተሰብን ግንዛቤ በማስፋት ፣አጥፊዎችን ለህግ በማቅረብ  በቁርጠኝነት ይሰራል፡፡

" አሁን ያለው ለውጥን ተከትሎ ምሁራን ወደ ሁሉም የስራ ዘርፍና የፖለቲካ አመራር በመምጣታቸው የተሻለ ሥራ ለመስራት ያስችለናል"ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዱር እንስሳት ልማት ባለሥልጣን ምክትል ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን መኮንን በሀገሪቱ በሚገኙ ፓርኮችና መጠለያዎች ሰው ሰራሽ ችግሮች እየደረሰባቸው እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

"በተለይ የባቢሌ ዝሆኖች መጠለያ በህገ-ወጥ ሰፈራ ሲወረር ዝሆኖቹ የሚሄዱበት በማጣት የሰው ህይወት እየጠፋና የሚሞቱ ዝሆኖች ቁጥር ከፍተኛ ሆኗል "ብለዋል፡፡

ሁሉም ትኩረት ሰጥቶ ዝሆኖቹንና መጠለያቸውን ከጥፋት መታደግ እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡

በ1962 ዓ.ም.  የተቋቋመው የባቢሌ ዝሆኖች መጠለያ ባለው 6ሺህ 982 ካሬ ኪሎ ሜትር ስፋት ውስጥ ከ320 በላይ ዝሆኖች እንደሚገኙበት ተገልጿል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም