ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በመንግስታቱ ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ውጤታማ ሥራ ሠርታለች - የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

አዲስ አበባ ታህሳስ 18/2011  ኢትዮጵያ በመንግሥታቱ ድርጅት ጸጥታው ምክር ቤት በተለዋጭ አባልነቷ ውጤታማ ሥራ ማከናወኗን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።

የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ በተሰጠው ትኩረት በተለይም አሁን በአገሪቱ እየተካሄደ ያለው ለውጥ በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ድጋፍ እንዲያገኝ አስችሏታል ነው ያሉት።  

የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አቶ መለስ ዓለም ዛሬ በሰጡት መግለጫ ኢትዮጵያ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ያስቀመጠቻቸውን መርህዎችና ዓላማዎች አሳክታለች ብለዋል።

ከገጽታ ግንባታ አኳያም ኢትዮጵያ በኢኮኖሚ ልማት፣ በቱሪዝም እና በሠላምና ፀጥታ ያበረከተችውን ሚና ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ለማስተዋወቅ ያደረገችውን ጥረት ጠቅሰዋል።

ለምስራቅ አፍሪካ በተለይም ለአፍሪካ ቀንድ አካባቢም ቅድሚያ በመስጠት የጸጥታ ሁኔታው እንዲሻሻል ሰርታለች፤ ጥረቷንም አጠናክራ እንደምትቀጥል አቋሟም አሳይታለች ነው ያሉት። 

ለዚህም እንደ አፍሪካ ተወካይነቷ፤ በጸጥታው ምክር ቤት የአህጉሪቱን ተወካይ በማስተባበር ምክር ቤቱ የአፍሪካን ጥቅም እንዲያራምድ መትጋቷን ገልጸዋል። 

የኤርትራ ማዕቀብ እንዲነሳና በደቡብ ሱዳን የመንግስታቱ ድርጅት ሥራ የተሰማራው የኢትዮጵያ ሠላም አስከባሪ ኃይል በየስድስት ወሩ የሚራዘምበት ጊዜ እንዲኖረው ጥረት ማድረጓንም ተናግረዋል።

በደቡብ ሱዳን የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ-መንግሥታት /ኢጋድ/ የሠላም ድርድር በምክር ቤቱ ድጋፍ እንዲያደርግ ከፍተኛ ቅስቀሳ ማድረጓንም ነው ቃል አቀባዩ ያስረዱት።

በመንግሥታቱ ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ከአፍረካ ኅብረት አቻ ተቋም ጋር ያለው ቅንጅታዊ አሰራር እንዲጠናከር ማስቻሉንም አብራርተዋል።

በጥቅሉም ኢትዮጵያ በምክር ቤቱ የነበራት የተለዋጭ አባልነት ቆይታዋ ስኬታማ መሆኑን ነው ቃል አቀባዩ የተናገሩት።

በአጠቃላይ ኢትዮጵያ በምክር ቤቱ አባላት በሚቀርቡ አጀንዳዎች ገለልተኛ፣ ሚዛናዊ እና የኢትዮጵያን ጥቅም መሰረት ያደረገ አቋም ማራመድ በመቻሏ ትርፋማ መሆኗን አረጋግጠዋል።

ኢትዮጵያ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከ1967 እስከ 68 እና ከ1989 እስከ 90 ድረስ በተለዋጭ አባልነት አገልግላለች።

ለሦስተኛ ጊዜ አባል የሆነችበት የአሁኑ አባልነቷም ታህሳስ 22 ቀን 2011 ዓ.ም ይጠናቀቃል፤ ኢትዮጵያን በመተካትም ደቡብ አፍሪካ የተለዋጭ አባልነቱን መቀመጫ ትይዛለች። 

በሌላ በኩል ስደተኞችን በተመለከተም ባለፉት ስድስት ወራት በተለያዩ መልኩ ወደ ውጭ አገራት የሄዱ 44 ሺህ 500 ኢትዮጵያዊያን ወደ አገራቸው መመለሳቸውን አንስተዋል።

በውጭ አገራት የሰሩበት ገንዘብ ሳይከፈላቸው የሚሰሩ ኢትዮጵያዊያን ሠራተኞችም ደሞዛቸውን በድርድር እንዲያገኙ ተደርጓል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም