የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ በቀሩት ጥቂት ቀናት ነጋዴዎች የንግድ ፈቃዳቸውን እንዲያሳድሱ አሳሰበ

150

አዲሰ አበባ ታህሳስ 18/2011 የአዲስ አበባ ከተማ ንግድ ቢሮ የንግድ ፈቃዳቸውን ያላሳደሱ ነጋዴዎች በቀሪዎቹ 12 ቀናት ውስጥ እድሳታቸውን እንዲያጠናቅቁ አሳሰበ።

የቢሮው የንግድ ምዝገባና ፍቃድ ዳይሬክተር አቶ ብርሃኑ ተገኝ እንደገለፁት በከተማዋ የንግድ ፈቃዳቸውን ያሳድሳሉ ተብለው ከሚጠበቁት 251 ሺህ 671 ነጋዴዎች መካከል እስካሁን እድሳት የፈፀሙት 158 ሺህ 320 ብቻ ናቸው።

ቢሮው በንግድ ምዝገባና ፍቃድ አዋጅ ቁጥር 980/2008 በተደነገገው መሰረት ከሐምሌ 1 እስከ ታህሰስ 30 ድረስ እድሳትና ምዝገባ የሚያከናውን መሆኑ ይታወቃል።

ይሁን እንጂ በተሰጠው ጊዜ እድሳታቸውን የማያጠናቅቁ ነጋዴዎች ከጥር 1 ጀምሮ ሲስተናገዱ 2 ሺህ 500 ብር ተጨማሪ ቅጣት ለመክፈል ይገደዳሉ።

እስከ ሰኔ 30 ቆይተው እድሳት ፈልገው የሚመጡ ነጋዴዎች ደግሞ በየወሩ 1ሺህ 500 ብር እየጨመረ በመሄድ በድምሩ የ10 ሺህ ብር ቅጣት እንደሚጠብቃቸው ዳይሬክተሩ ገልፀዋል።

በመሆኑም ነጋዴው ማህብረሰብ ከተጨማሪ ቅጣት ለመዳን በቀሪዎቹ ጥቂት ቀናት እድሳቱን እንዲያከናውን አሳስበዋል።

የእድሳት ጊዜው ሊጠናቀቅ ጥቂት ቀናት የቀሩት በመሆኑ መስተጓጎል እንዳይፈጠር በሚል ቢሮው ከስራ ቀናት በተጨማሪ ቅዳሜና እሁድም አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን አቶ ብርሃኑ ገልፀዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ ንግድ ቢሮ ከሐምሌ 1 ቀን 2010 ዓ.ም ጀምሮ ከእድሳት በተጨማሪ ለ30 ሺህ ነጋዴዎች አዲስ የንግድ ፍቃድ መስጠቱን ከቢሮው የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም