የሀዋሳ ቅዱስ ገብርኤል ንግስ በዓል በሰላም እንዲጠናቀቅ ዝግጅት መደረጉን ፖሊስ አስታወቀ - ኢዜአ አማርኛ
የሀዋሳ ቅዱስ ገብርኤል ንግስ በዓል በሰላም እንዲጠናቀቅ ዝግጅት መደረጉን ፖሊስ አስታወቀ
ሀዋሳ ታህሳስ 18/2011 ዓመታዊው የሀዋሰ ቅዱስ ገብርኤል ንግስ በዓል በሰላም እንዲጠናቀቅ ዝግጅት ማድረጉን ፖሊስ አስታወቀ፡፡
የከተማ አስተዳደሩ ፖሊስ አዛዥ ኮማንደር መስፍን ዴቢሶ ለኢዜአ እንደተናገሩት በዓሉ በሰላም እንዲጠናቀቅ መደበኛ ፖሊስ ከልዩ ሃይል፣ መከላከያና ፌደራል ፖሊስ ጋር በቅንጀት መስራት የሚያስችል ኮማንድ ፖስት ተቋቁሟል፡፡
በከተማዋ የስጋት ቀጠናዎች ተለይተው ጥበቃ እንደሚደረግባቸው የተናገሩት ፖሊስ አዛዡ ''እንግዶች የሚያርፉባቸውና መኪኖች የሚቆምባቸው ቦታዎች ከዝግጅቶቹ ውስጥ ይጠቀሳሉ'' ብለዋል፡፡
በበዓል ወቅት ሊያጋጥሙ የሚችሉ የስርቆትና ሌሎችም ወንጀሎች አፋጣኝ ምላሽ መስጠት የሚያስችል ጊዜያዊ ችሎት መቋቋሙንም ጠቁመዋል፡፡
የትራፊክ መጨናነቅ እንዳይፈጠር ከነገ ጀምሮ ከዋርካ አደባባይ፣ ከሎጊታ፣ ከጤና ቢሮና ከፒያሳ ወደ ገብርኤል የሚወስዱ መንገዶች ለተሸከርካሪ ዝግ እንደሚሆኑም አስታውቀዋል፡፡
ለበዓሉ ወደ ከተማው የሚገቡ ተሸከርካሪዎችም በሃዋሳ አለም አቀፍ ስታዲየም፣ ሚሊኒየም አዳራሽ ግራና ቀኝ ባሉ ቦታዎችና ቤተክህነት ትምህርት ቤት ቢቆሙ በቂ ጥበቃ ይደረግላቸዋል፡፡
በዓሉን ለማክበር ወደ ከተማዋ ለሚገቡ ምእመናንም የከተማዋ ነዋሪዎች በተለመደ የእንግዳ አቀባበል ማስተናገድ እንደሚገባው መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡