ድሬዳዋ ከነማ ከደቡብ ፖሊስ አቻ ተለያየ

76

ድሬዳዋ ታሀሳስ18/2011 የኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ ሁለተኛ ሳምንት ተስተካካይ ጨዋታ ድሬዳዋ ከነማ በሜዳው ከደቡብ ፖሊስ ጋር አንድ ለአንድ ተለያየ።

በድሬዳዋ ስታዲዬም የተካሄደው ጨዋታ ቀዝቀዝ ብሎ በጀመረው የመጀመሪያ አጋማሽ የደቡብ ፖሊሱ ዘሪሁን አሸቦ በሰባተኛው ደቂቃ ባስቆጠረው ግብ ክለቡ መሪ ቢሆንም፤ ከሁለት ደቂቃ በኋላ ድሬዳዋ ከነማ በሂታሞኒ ኬሞኒ ግብ አቻ ሆኗል፡፡

ድሬዳዋ ከነማ ከዕረፍት በኋላ ጨዋታውን ተቆጣጥሮ ጫና ፈጥሮ የተጫወተ ሲሆን፤ በአጨራረስ ድክመትና በደቡብ ፖሊስ ግብ ጠባቂ ብቃት ሙከራዎቹ  ሳይሳኩ ቀርተዋል፡፡

የደቡብ ፖሊስ ተጫዋቾች የጨዋታውን ውበትና ፍሰት በማበላሸታቸው አራት ተጫዋቾች ለቢጫ ካርድ ተዳርገዋል፡፡

ከጨዋታው በኋላ የድሬዳዋ ከነማ ዋና አሰልጣኝ ዮሐንስ ሣህሌ የተሻለ ጨዋታና ግብ የሚሆኑ ዕድሎችን ፈጥረናል ብለዋል፡፡

''በታደሰው ሜዳችንና በደጋፊዎቻችን ፊት ባደረግነው የመጀመሪያ ጨዋታ ተጫዋቾቹ ለማሸነፍ የነበራቸው ከፍተኛ ጉጉት በስሜት ያደረጓቸው በመሆኑ ያለቀላቸውን ከሰባት በላይ ግብ የሚሆኑ ኳሶች ስተዋል'' ብለዋል፡፡

''እንደ ነበረን ብቃት ማሸነፍ ይገባን ነበር፤ አንዳንዴ እንዲህ ተጫውተህ  ልትሸነፍ ትችላለህ፤ እግር ኳስ እንዲህ ነው'' ሲሉም ተናግረዋል፡፡

በመጀመሪያው ግማሽ ተጨማሪ ግብ የማግባትና ጨዋታውን የማሸነፍ አጋጣሚ ነበረን፤ የተቆጠረብን ግብ ራሳችን በፈጠርነው ስህተት  ነበር ያሉት ደግሞ የደቡብ ፖሊሱ ምክትል አሰልጣኝ አቶ ያለው ተመስገን ናቸው፡፡

ከተደጋጋሚ ሽንፈት በኋላ ያገኙት አንድ ነጥብ በአዳማ ለሚኖራቸው ጨዋታ መነቃቃት እንደሚፈጥርላቸው እምነታቸውን ገልጸዋል፡፡

የታደሰው የድሬዳዋ ሜዳ ለጨዋታ የተመቸና ለሌሎችም በአርአያነት ይጠቀሳል ብለዋል፡፡

የስፖርት ደጋፊውም ጥሩ ለተጫወተ ቡድን የሚያሳየው ድጋፍ የሚያበረታታና የሚደነቅ መሆኑን ነው አሰልጣኝ ያለው የገለጹት፡፡

የድሬዳዋ ከነማ ደጋፊ አቶ ሙስጠፋ ዓሊ በዚህ ደጋፊ፣ በዚህ ያማረ ሜዳ ይህን ሁሉ ጎል ስተው አቻ መውጣታቸው ያስቆጫል ፤ ያስከፋል ብለዋል፡፡

''በሚቀጥለው ሳምንት ከሜዳችን ውጪ ከወላይታ ዲቻ ጋር ለሚኖረን ጨዋታ ቡድኑን በሥነ-ልቡና ማጠንከር ይገባል'' ሲሉም ጨምረው ገልጸዋል፡፡ 

ድሬዳዋ ከነማ ሁለት ቀሪ ተስተካካይ ጨዋታዎች ከመከላከያና ከጅማ አባጅፋር ጋር ያሉት ሲሆን፣ በሳምንቱ መጨረሻ ወደ ሶዶ ተጉዞ  ከወላይታ ዲቻ ጋር ይጫወታል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም