የስራ ክቡርነት በማረጋገጥና የአሰሪና ሰራተኛ ግንኙነት በማጠናከር ውጤታማ ለመሆን መስራት ያስፈልጋል-- ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር - ኢዜአ አማርኛ
የስራ ክቡርነት በማረጋገጥና የአሰሪና ሰራተኛ ግንኙነት በማጠናከር ውጤታማ ለመሆን መስራት ያስፈልጋል-- ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር
አዲስ አበባ ታህሳስ 18/2011 የስራ ክቡርነት የተረጋገጠበትና የአሰሪና ሰራተኛ ግንኙነት የተከበረበት አገር ወደ ብልጽግና ከመገስገስ የሚገታው ኃይል ስለማይኖር ለተግባራዊነቱ ሁሉም በቁርጠኝነት መንቀሳቀስ እንደሚኖርበት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን አስገነዘቡ።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ በአገር አቀፍ ደረጃ ለመጀመሪያ ጊዜ እየተካሄደ በሚገኘው የአሰሪና ሰራተኛ ጉባኤ ላይ የመክፈቻ ንግግር አድረገዋል።
በወቅቱም የስራ ክቡርነትን ማረጋገጥና የአሰሪና ሰራተኛን ግንኙነት ማጠናከር ወደ ብልጽግና የሚደረገውን ግስጋሴ እንደሚያፋጥነው ነው የተናገሩት።
ጉባኤው በግብርናውና በኢንዱስትሪው ዘርፍ የተሳካ ስራ በማከናወን ረገድ ወጣቱን ተሳታፊ ያደረገ የስራ ሁኔታን ለመፍጠር ያለመ መሆኑም ተመልክቷል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ እንደገለጹት፤ አሰሪዎች ከሰራተኞቻቸው ጋር ያላቸውን መልካም ግንኙነት በማጎልበት ጠንካራ ተግባራትን በማከናወን ኢኮኖሚን ወደ ላቀ ደረጃ ማድረስም ያስፈልጋል።
በእስካሁኑ የእድገት ጉዟችን ስኬትን የተጎናጸፍንባቸው መስኮችና ውድቀትን ባስተናገድንባቸው ዘርፎች ለስራ የምንሰጠው ዋጋ ከውጤት ደጃፍ እንዴት እንደሚያቀራርብና እንዴት እንደሚያራርቀን በሰፊው ተምረንበታል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በእድገት ቅብብሎሽ ወደ ኢንዱሰትሪው ዘርፍ ለመቀላቀል በምናደርገው ርብርብ የአሰሪና ሰራተኛ ግንኙነት የተከበረበት አገር ለማምጣት ሁላችንም ቁርጠኛ ሆነን መንቀሳቀስ ይኖርብናል ብለዋል፡፡
የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትሯ ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ በበኩላቸው፤ ጉባኤው ወጣቶችን በተለያዩ የስራ ዘርፎች እንዲሰማሩ ለማስቻል መከናወን ያለበት ቅድመ ሁኔታ ለማመቻቸት እድል ለመፍጠር ያስችላል።
በተለይም አገሪቷ ከግብርናው ወደ ኢንዱስትሪው ዘርፍ ለምታደርገው ሽግግር በአሰሪና ሰራተኛ ላይ ያተኮሩ ስራዎች እንዲከናወኑ ለማድረግ በማሻሻያ ስራዎች አተኩሮ መስራት ተገቢ መሆኑን ነው ያመለከቱት።
አገራችን ከግብርናው ዘርፍ ወደ ኢንዱስትሪው ዘርፍ ለምታደርገው የኢኮኖሚ ሽግግር ትልቅ አቅመ እንደሆነና በዚህም የሽግግር ሂደት ያለንን የሰው ኃብት በተገቢው ለመጠቀም በተለይ የአሰሪና ሰራተኛው ጉዳይ ከፍተኛ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው መሆኑን አስረድተዋል
በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ሰራተኛ ማህበራት ኮንፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ካሳሁን ፉሎ በበኩላቸው፤ ሰራተኞች በህገ መንግስቱ መሰረት የመደራጀት ሙሉ መብት ቢኖራቸውም በተደራጁ ሰራተኞች ላይ የህግ ጥሰት እየተፈጸመባቸው እንደሆነ አብራርተዋል።
ሰራተኞች ከስራቸው በአላስፈላጊ ሁኔታ እንዲሰናበቱ እየተደረገ መሆኑንም ነው ያመለከቱት።
የተረጋጋ የኢንዱስትሪ ሰላም እንዲኖርና ኢንቨስተመንት ተስፋፍቶ ዘላቂ ልማት ሊረጋገጥ የሚችለው የአሰሪና የሰራተኛው መብት ሳይሸራረፉ እኩል ሲከበሩ ብቻ ነው።
የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ አሰሪዎች ኮንፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ታደለ ይመር እንደገለጹት አስተማማኝና ዘላቂ የኢንዱሰትሪ ሰላም ለማስፈን የአሰሪና ሰራተኛ ሚና ትልቁን ድርሻ ይወስዳል።
በዚህም አሰሪውም ሆነ ሰራተኛው የሚጠበቅበትን ግዴታ ከተወጣ "ልማትና እድገት የሰፈነበት የአሰሪና ሰራተኛ አገር መገንባት ቀላል ነው"ብለዋለል።
የአይ ኤል ኦ ተወካይ ወይዘሮ ቅድስት ጫላ፤ የአሰሪና ሰራተኛ የስራ ሁኔታን በማሻሻል ዓለም የደረሰበት ደረጃ ለማድረስ እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል።
የአገሪቷን የሥራ ሁኔታ በተለይም የሰራተኛውንና የአሰሪውን ግንኙነት ለማጎልበት እንደሁልጊዜው ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስረድተዋል።
ጉባኤው ''የኢንዱስትሪ ሰላም ለአካታችና ለዘላቂ ሰላም''በሚል መሪ ሃሳብ የሚካሄድ ነው።