በየሳምንቱ የመርሃ ግብር ማስተካካያ የማያጣው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ - ኢዜአ አማርኛ
በየሳምንቱ የመርሃ ግብር ማስተካካያ የማያጣው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ
አዲስ አበባ ታህሳስ 17/2011 የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በሶስት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች የውድድር መርሃ ግብር ማስተካከያ ማድረጉን አስታወቀ።
በየሳምንቱ የመርሃ ግብር ማስተካከያ የማያጣው የሊጉ ውድድር በዘጠነኛ ሳምንት ሁለት ጨዋታዎች ላይ የቀን ለውጥ አድርጓል።
ፌዴሬሽኑ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በሰጠው መግለጫ እንዳስታወቀው፤ ታህሳስ 27 ቀን 2011 ዓ.ም በሃዋሳ ዓለም አቀፍ ስታዲየም ሃዋሳ ከተማ ከጅማ አባ ጅፋር ከቀኑ ዘጠኝ ሰአት ሊካሄድ የነበረው ጨዋታ ወደ ታህሳስ 29 ቀን 2011 ዓ.ም ዘጠኝ ሰአት እንዲተላለፍ ተደርጓል።
በመቐለ ዓለም አቀፍ ስታዲየም ታህሳስ 27 ቀን 2011 ዓ.ም መቐለ ሰብዓ እንደርታ ከሲዳማ ቡና ከቀኑ ዘጠኝ ሰአት ሊያደርጉት የነበረው ጨዋታ ታህሳስ 29 ቀን 2011 ዓ.ም ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት እንዲደረግ ተወስኗል።
በሌላ በኩል ጅማ አባ ጅፋር በአፍሪካ ሻምፒዮንስ ሊግ ከግብጹ አል ሃሊ በነበረበት የመልስ ጨዋታ የተራዘመው የሲዳማ ቡናና የጅማ አባ ጅፋር የሰባተኛ ሳምንት ጨዋታ ታህሳስ 25 ቀን 2011 ዓ.ም ከቀኑ 10 ሰዓት በሃዋሳ ዓለም አቀፍ ስታዲየም ይካሄዳል።
በ2011 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ በየሳምንቱ በሚደረጉ ጨዋታዎች ላይ የመርሃ ግብር ለውጥ ማድረግ የተለመደ ሆኗል።
ገና ከጅምሩ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎችን በወጣላቸው መርሃ ግብር ማካሄድ ፈተና የሆነበት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በተለያዩ ምክንያቶች ጨዋታዎች ማራዘሙ በክለቦች በኩል ቅሬታ እያስነሳበት ይገኛል።
የመርሃ ግብሮች መቆራረጥና በወጣላቸው መርሃ ግብር አለመካሄድ የዘንድሮው ዓመት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ዋና ገጽታ ሆኗል ማለት ይቻላል።