ግንቦት ሰባት ለውጡ እንዳይደናቀፍ ከመንግስትና ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር እሰራለሁ አለ - ኢዜአ አማርኛ
ግንቦት ሰባት ለውጡ እንዳይደናቀፍ ከመንግስትና ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር እሰራለሁ አለ
አዲስ አበባ ታህሳስ 17/2011በኢትዮጵያ የተጀመረው ለውጥ እንዳይደናቀፍ ከመንግስትና ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር ለመስራት ቁርጠኛ መሆኑን የአርበኞች ግንቦት ሰባት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ ንቅናቄ አስታወቀ።
በአገር ውስጥ ያሉ አባላቱን ትጥቅ ለማስፈታት ዝግጁ መሆኑንም ተናግሯል።
የንቅናቄው ዋና ጸሐፊ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ በወቅታዊ ጉዳይ ላይ በሰጡት መግለጫ እንዳሉት በአገሪቱ አመጽ ተወግዶ ፖለቲካውን በሰላማዊና በሰለጠነ መንገድ ለማካሄድ የተጀመረው ተግባር እንዳይደናቀፍ ንቅናቄው የበኩሉን ጥረት ያደርጋል።
በመሳሪያ ኃይል ይንቀሳቀሱ የነበሩ አባላቱን ትጥቅ አስፈትቶ ወደ አገር ቤት በማስገባትና ትጥቅ ያልፈቱትንም ወደ መስመር ለማስገባት ከመንግስት ጋር በመስራት ላይ ይገኛል ነው ያሉት።
ይህን ያደረገው "አመፅና ትጥቅን መሰረት ያደረገ ትግል ኢትዮጵያን ወደ ውድመት ከመምራት ባሻገር ጥቅም እንደሌለው በማመን ነው" ብለዋል።
ብዝሃነትን በምታስተናግድ አገር የአመጽ ሳይሆን ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ወሳኝ መሆኑን ያወሱት አቶ አንዳርጋቸው ግጭቶችን ማስቆም የመንግስት ኃላፊነት ቢሆንም የፖለቲካ ፓርቲዎችም ሚናቸውን መወጣት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።
''ሰላም ማከበር ህግ ማስከበር የመንግስት ኃላፊነት ቢሆንም በእኛ እምነት የመንግስት ብቻ ሃላፊነት ተብሎ ባለንበት ሁኔታ ሊተው አይችልም። በዚህ አገር ላይ ሌላ አማራጭ የለም ማንኛውም የፖለቲካ ድርጅት ሰላማዊና ህጋዊ በሆነ መንገድ ብቻ ነው መንቀሳቀስ የሚኖርበት ብለን የምናምነው ሰላማዊና ህጋዊ በሆነ መንገድ ሁሉም ድርጅቶች እንዲንቀሳቀሱ ሁኔታዎችን ስልጣን ላይ ያለው መንግስት በተወሰነ ደረጃ አመቻችቷል።”
“ችግሮች ካሉ ከፖለቲካ ድርጅቶች ጋር እየተነጋጋሩ እነዚህን ችግሮች እያቃለሉ የፖለቲካ ድርጅቶችም ማወቅ ያለባቸው ሁኔታዎች እንዲስተካካሉ የተጀመሩ እንጂ ተስተካካለው ያላለቁ መሆናቸውን አውቀው ለውጥ ከሚያራምደው መንግስት ጋር እየተነጋጋሩ መሄድ ነው እኛም የምናደርገው ይሄን ነው። '' ብለዋል፡፡
ንቅናቄው መንግስት ያደረገውን የሰላም ጥሪ ተከትሎ በኤርትራ በረሃ የነበሩ 300 ወታደሮችን ትጥቅ አስፈትቶ ወደ አገር ቤት መምጣቱን አስታውቀዋል።
በአገር ቤት ያሉና ትጥቅ ያልፈቱ 550 ወታደሮቹን ለማስፈታት ዝግጁ እንደሆነና የመንግስትን ምላሽ በመጠበቅ ላይ መሆኑን ተናግረዋል።
በመንግስት የተቀየሰው ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ግቡን እንዲመታ ፓርቲው ለህግ መከበር ከቆሙ ተፎካካሪ ፓርቲዎች፣ ከመንግስትና ከአባላቱ ጋር እንደሚሰራም አስታውቀዋል።
አባላትና ደጋፊዎች የአመጽ ስራዎች ላይ እንዳይሳተፉ መመሪያ በመስጠት እስካሁን የተፈጠረ ችግር እንደሌለ ገልጸው በቀጣይም ለህግ የበላይነት መከበር እና ለሰላም ያላቸውን ሚና አጠናክረው እንዲቀጥሉ ይደረጋል ነው ያሉት።
በንቅናቄው ስም ጥቃት የሚፈፅሙ አካላት ቢኖሩ ለመንግስት አሳልፎ እንደሚሰጥም ዋና ጸሐፊው ተናግረዋል።
የአርበኞች ግንቦት ሰባት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ ንቅናቄ ጳጉሜን 4 ቀን 2010 ዓም ወደ አገር ቤት መግባቱ ይታወሳል።