ቀጥታ፡

የንግድና ኢንቨስትመንት ዘርፍ ላይ የማሻሻያ ተግባራት ሊከናወኑ ነው

አዲስ አበባ ታህሳስ 17/2011 ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ኢትዮጵያ አሁን ካለችበት ዝቅተኛ የንግድና ኢንቨስትመንት ምቹነት ሁኔታ የማሻሻያ ተግባራት ሊከናወኑ መሆኑን ገለፁ።

በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ የሚመራና ከተለያዩ የዘርፍ መስሪያ ቤቶች የተውጣጣ የንግድና ኢንቨስትመንት ምቹነት ሁኔታ ለመፍጠር ብሄራዊ መርሃ ግብር  የሚመራ ኮሜቴ ተቋቁሟል።

ብሄራዊ መርሃ-ግብሩም በ10 አስፈፃሚ ተቋማት የሚተገበሩ ሲሆኑ  80 ልዩ ተግባራትን ይዟል፡፡

ይህ ብሄራዊ መርሃግብር በጠቅላይ ሚኒስትሩ ተቆጣጣሪነት የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ፖሊሲና አፈፃፀም ክፍል ክትትል እየተደረገበት የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን የሚያስተባብረው ይሆናል፡፡

ኮሜቴው ዛሬ ባደረገው ስብሰባ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ  እንዳሉት በዘርፉ ያለውን ደካማ ፣ አስቸጋሪና ተገማችነት የሌለው አሰራር በመውጣት ለግል ባለሃብቱ በተለይም ደግሞ አዲስ ወደ ዘርፉ ለሚገቡ አልሚዎች ምቹ ማድረግ ያስፈልጋል።

ኢትዮጵያ “በንግድና ኢንቨስትመንት ያላት ምቹነት በጣም ዝቅተኛ ነው” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ይህም ከ190 አገሮች 159ኛ ደረጃ ላይ እንድትቀመጥ አድርጓታል።

በዚህ መሰረት ጎረቤት አገር ኬኒያ በዘርፉ ምቹነት 61ኛ ደረጃ ላይ ስትገኝ ፤ ሩዋንዳም 29ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች።

ኢትዮጵያ በርካታ የኢንቨስትመንት አማራጮችና መልካም አጋጣሚዎች እንዳላት ያስታወሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፤ ደካማና ውጣ ውረድ የበዛበት አሰራር ምክንያት በዝቅተኛ ደረጃ ላይ መገኘቷን ገልፀዋል።

ከዚህ አኳያ ዘርፉ ማሻሻያ ሊደረግበት ግድ በመሆኑ “በቀጣዮቹ 100 ቀናት ውስጥ የአሰራርና ህግ ማሻሻያ በማድረግ አስፈልጓል” ብለዋል።

በመሆኑም የባንኮች የአሰራርና የብድር አሰጣጥ ስርአት ፣ የንግድ ህግ ፣ የግብር አሰባሰብ፣ የሃይል አቅርቦትና ሌሎንም ለዘርፉ ዘመናዊነት የሚያግዙ ማሻሻያዎችን በማድረግ ወደ ስራ ይገባል።

ይህንንም ለማሳካት የአጭር፣ መካከለኛና ረጅም ጊዜ እቅድ በማዘጋጀት ማሻሻያው እውን እንዲሆን ይሰራል።

የአሰራር ማሻሻያው በየወሩ እየተገመገመ አገሪቷ አሁን ካለችበት የምቹነት ደረጃ በማሻሻል ከ100 በታች እንዲሆን ማድረግ እንደሚያስፈልግ አጽንኦት ሰጥተዋል።

እንደጠቅላይ ሚኒስትሩ ገለጻ ፤ ይህ እውን ሲሆን በርካታ ኢንቨስተሮችን ከመሳብ በተጨማሪ ኢኮኖሚው ለውጥ እንዲያስመዘግብም ያግዛል።

በውይይቱ ወቅት የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የህግ አማካሪ አበበ አበባየሁ የውይይት መነሻ ፅሁፍ አቅርበዋል።

በፅሁፋቸውም ቢዝነስ ለመስራት የሚያስፈልጉ 10 መሰረታዊ መመዘኛዎች ያሏቸውን ነጥቦች እንዲሁም የኢንቨስትመንት ማሻሻያ ሃሳቦችን አካተው አቅርበዋል።

ከመመዘኛዎቹ መካከል የግንባታ ፈቃድ፣ የሃይልና ብድር አቅርቦት እንዲሁም የጉምሩክና ሌሎችንም ጠቅሰዋል።

በኢትዮጵያ አሁን ያለውን የንግድና ኢንቨስትመንት አሰራር ለማዘመን የጉምሩክ፣ የንግድ፣ የብድር አቅርቦት፣ የገቢ አከፋፈል እንዲሁም ሌሎች አሰራሮችን ቀልጣፋና በኤሌክትሮኒክ የታገዘ አሰራርን መፍጠር እንደሚያስፈልግ ነው ያመለከቱት።

የኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ፍፁም አረጋ በበኩላቸው የግሉ ዘርፍ ፈጣን አገልግሎት እንዲያገኝና የኢኮኖሚ እድገቱ ቀጣይነት እንዲኖረው ማሻሻያ ማስፈለጉን ተናግረዋል።

በአገሪቷ በፍትህና በዲሞክራሲ ተቋማት በተደረገው ማሻሻያ እየታየ ያለው ለውጥ በኢንቨስትመንቱም ተጨባጭ ለውጥ ያመጣል ተብሎ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም