የአገልግሎት አሰጣጥና የትምህርት ጫና እንዳለባቸው በአሶሳ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ተናገሩ

112
አሶሳ ታህሳስ 17/2011 በአሶሳ ዩኒቨርሲቲ ተቋርጦ የነበረው ትምህርት ቢጀመርም የአገልግሎት አሰጣጥና የትምህርት ጫና ችግር እንዳለባቸው የአሶሳ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ተናገሩ፡፡ አስተያየታቸውን የሰጡ የዩኒቨርስቲው ተማሪዎች ለኢዜአ እንዳሉት በተቋሙ ተፈጥሮ በነበረው  ግጭት የተቋረጠው መማር ማስተማር እንደገና ተጀምሯል፡፡ የአራተኛ ዓመት ሂሳብ አያያዝ ተማሪ አበበች አምሳሉ የግቢው ጸጥታ ሁኔታ ከጊዜ ወደ ጊዜ መሻሻል እየታየበት መምጣቱን ተናግራለች፡፡ ግጭቱን ሸሽተው የሄዱ የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎችም አብዛኞቹ ወደ ግቢው መመለሳቸውን የተናገረው ደግሞ የሶስተኛ ዓመት የቅየሳ ምህድስና ተማሪ ሁሴን በድሩ ነው፡፡ " ወደ ዩኒቨርሲቲው ያልመጡ ጥቂት ተማሪዎች ቢሆኑ በትራንስፖርት እጥረት ካልሆነ ወደ ዩኒቨርሲቲው ተመልሰው የመማር ፍላጎት አላቸው" ብሏል፡፡ በዩኒቨርሲቲው ትምህርት መሰጠት ቢጀምርም አሁንም ያልተፈቱ ችግሮች በመኖራቸው ትኩረት ሊሰጣቸው እንደሚገባ ተማሪዎቹ ጠቁመዋል፡፡ ተማሪ ደግነት ይበልጣል በበኩሉ በግጭቱ ሸሽተው ከሄዱ በኋላ ሲመለሱ ማደሪያ ያላገኙ የቀን ተማሪዎች እንዳሉ ተናግሯል፡፡ ከሁሉም ተማሪ ባይሆንም ስልክ፣ ኮምፒዩተር እና ልብስ የጠፋባቸው ተማሪዎች እንዳሉ የገለጹው ደግሞ  ተማሪ አዶላ ጃርሶ ነው፡፡ ሌላው ተማሪ ሁሴን በድሩ " በግጭቱ ወቅት የጠፋውን የትምህርት ጊዜ ለማካካስ ሲባል በአንዳንድ መምህራን የሚሰጠው በአንድ ክፍለ ጌዜ እስከ ሶስት ምዕራፍ የሚደርስ ትምህርት ጫና እየፈጠረብን ነው" ብሏል፡፡ ከዚህ ይልቅ በቂ ጊዜ ተሰጥቷቸው  ትምህርታቸውን በተረጋጋ ሁኔታ መከታታል እንደሚሻል ተናግሯል፡፡ የአሶሳ ዩኒቨርሲቲ ተወካይ ዶክተር ኃይማኖት ዲሳሳ ተቋሙ የመማር መስተማር ሥራውን ወደ ነበረበት  ሠላማዊ ሁኔታ ለመመለስ ጥረት እያደረገ መሆኑን ገልጸው "እየተረጋጋ በመምጣቱ አሁን ከ95 በመቶ በላይ የሚሆኑ ተማሪዎች ወደ ግቢው ተመልሰው ትምህርት ጀምረዋል" ብለዋል፡፡ በዩኒቨርሲቲው  በተለይ የምግብ፣ መኝታ እና መሰል አገልግሎቶች ላይ የሚታዩ ችግሮችን ለማስተካከል በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ ተማሪዎቹ ያነሱትን የተማሪዎች ማዳሪያ ስብጥር እና ድልድል በተመለከተ ለማረጋጋቱ ሥራ ቅድሚያ በመሰጡ የተፈጠረ ክፍተት በመሆኑ እንደሚስተካከል ገልጸዋል፡፡ በግጭቱ ወቅት የተማሪዎች ብቻ ሳይሆን የዩኒቨርሲቲው ንብረት ጉዳት እንደደረሰበት የጠቀሱት ዶክተር ኃይማኖት ሶስት ሺህ 500 አንሶላዎች ተገዝተው ግማሽ ያህሉ መከፋፈላቸውን አመልክተዋል፡፡ እርሳቸው እንዳሉት  ንብረት ሳይጠፋባቸው ያመለከቱ አንዳንድ ተማሪዎች በመኖራው ዩኒቨርሲቲው ጉዳዩን አጣርቶ መፍትሄ ለመስጠት የሚያደርገውን ሥራ አዘግይቶታል፡፡ " የባከነውን የትምህርት ጊዜ ለማካካስ የወጣውን ፕሮግራም በተማሪዎች ላይ ጫና አሳድሮ ከሆነ የዩኒቨርሲቲው ሴኔት እንደገና የማይፈትሽበት ምክንያት የለም "ብለዋል፡፡ የተማሪዎች ህብረት ዩኒቨርሲቲው ከተማሪዎች ጋር በቀጥታ የሚገናኝበት እንደሆነ የገለጹት ዶክተር ኃይማኖት ህብረቱ የተጠናከረ አለመሆኑ ያስከተለው ችግር እንዳለ ተናግረዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ሁሉንም የሚወክል የተማሪዎች ህብረት ለማቋቋም ኮሚቴ ተዋቅሮ እየተሠራ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡ ዩኒቨርስቲው በግጭቱ ወቅት ህይወታቸውን ላጡ  ሶስት ቤተሰቦች 240 ሺህ ብር ድጋፍ ማድረጉን ጠቅሰዋል፡፡ ተማሪዎች የመጡበትን ዓላማ ለማሳካት እንዲጥሩ እና ቤተሰቦቻውም ምክር ከመስጠት ጀምሮ ትምህርታቸውን በአግባቡ እንዲከታተሉ በመደገፍ የዩኒቨርሲቲውን ጥረት እንዲያግዙ ዶክተር ኃይማኖት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡ በ2004ዓ.ም. የተቋቋመው የአሶሳ ዩኒቨርሲቲ 10 ሺህ የሚጠጉ ተማሪዎች እንዳሉት ተመልክቷል፡፡    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም