ቀጥታ፡

የሰላም አምባሳደር እናቶች በፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች ላይ በመገኘት መልዕክት ሊያስተላልፉ ነው

አዲስ አበባ ታህሳስ 16/2011 የሰላም አምባሳደር እናቶች ነገና ከነገ በስቲያ በአዲስ አበባ ስታዲየም በሚደረጉ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ተስተካካይ ጨዋታዎች ላይ በመገኘት የሰላም መልዕክት ሊያስተላልፉ ነው። ነገ ኢትዮጵያ ቡና ከወልዋሎ አዲግራት ዩንቨርስቲ ከነገ በስቲያ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከጅማ አባጅፋር ጨዋታቸውን በተመሳሳይ 11:00 ያደርጋሉ። የሰላም አምባሳደር እናቶች በሁለቱም ቀን ጨዋታዎች ከቀኑ 10:30 እስከ 11:00 ሰዓት  በአዲስ አበባ ስታዲየም በመገኘት የሰላም መልእክት እንደሚያስተላልፉ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታውቋል። በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የስፖርታዊ ጨዋነት መጓደል በእግር ኳሱ ላይ መጥፎ ጥላ ከማጥላቱ ባለፈ በአጠቃላይ እግር ኳሱ እድገት ላይ ተጽእኖ እያሳደረ ይገኛል። በ2010 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የውድድር ዓመት ችግሩ ተባብሶ የታየበት ጊዜም ነበር። በዘንድሮው የውድድር ዓመትም በአዲስ አበባ ስታዲየም ቅዱስ ጊዮርጊስና ሃዋሳ ከተማ የሚያደርጉት ጨዋታ ሳይጀመር በሁለቱ ክለቦች መካከል በተነሳው ግጭት ጨዋታው በማግስቱ በዝግ ሜዳ እንዲካሄድ አስገድዶም ነበር። የእግር ኳሱ ቤተሰብ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ስፖርታዊ ጨዋነት መጓደል ተጠያቂ የሚሆኑ አካላት ላይ ጥብቅ እርምጃ እንዲወስድና ክለቦችም ደጋፊዎቻችን እንዲያስተምሩና አጥፊውንም እንዲያጋልጡ በተደጋጋሚ ተነስቷል። "በአገሪቷ አንዳንድ አካባቢዎች የሚሰማው የእርስ በርስ ግጭትና ማፈናቀል አሰጋን፣ አስጨነቀን" በማለት ሰላም እንዲሰፍን ጥረት እያደረጉ የሚገኙት የሰላም አምባሳደር እናቶች ወደ እግር ኳሱ በመምጣት መልዕክት ማስተላለፋቸው መልካም አጋጣሚ ነው። የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የስፖርታዊ ጨዋነት እንዲሰፍን "ልዩ ትኩረት ሰጥቼ እሰራለሁ" ቢልም በተለያዩ አጋጣሚዎች የሚታዩት የስፖርታዊ ጨዋነት መጓደሎች ጉዳዩን "ውሃ ቅዳ ውሃ መልስ" አድርጎበታል።          
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም