ቀጥታ፡

ሰው ሰራሽ ሃይቁ ዓሳ አሳ በማስገር አማራጭ የገቢ ምንጭ ሆኖናል- የዋግህምራ ዞን ነዋሪዎች

ሰቆጣ ግንቦት 16/2010 በዋግህምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን በሚገኘው ሰው ሰራሽ ሃይቅ ዓሳ በማስገር  ተጨማሪ ገቢ እያገኙ መሆናቸውን የአካባቢው  አስተያየት ሰጪዎች ተናገሩ፡፡ በሰው ሰራሽ ሃይቁ ከ2ሺህ 400 በላይ  አስጋሪዎች  ተደራጅተው  በአሳ  ማስገር  ስራ  ተሰማርተዋል፡፡ ከሶስት  ዓመት ወዲህ በማህበር ተደራጅተው በአሳ ማስገር ከተሰማሩት መካከል በአበርገሌ  ወረዳ   የቀበሌ 14   ነዋሪው ወጣት  አዲሱ  ሃይሌ  ለኢዜአ እንዳለው   አካባቢው ዝናብ አጠርና በምግብ ዋስትና የሚደገፍ  ነው፡፡ ቀደም ብሎ በቀን ስራ ይተዳደር እንደነበር አስታውሶ  200 ሆነው በመደራጀት በአሳ  ማስገር  ተሰማርተው ውጤታማ መሆናቸውን ተናግሯል። በዘርፉ የተሻለ  ገቢ  እያገኙ መሆናቸውን ጠቅሶ በግሉ በኒሯቅ  ከተማ  መኖሪያ ቤት  መገንባት እንደቻለ ገልጿል፡፡ ምርቱን ከአካባቢው አልፎ ወደ ሌሎች አካባቢዎች በመውሰድ በተሻለ ዋጋ ለመሸጥ የገበያ ትስስር ፈጥረው ለማቅረብ ዝግጅት  እያደረጉ  ይገኛሉ፡፡ አቶ  አምባየ  አማረ  የተባሉት ነዋሪ በበኩላቸው አካባቢያቸው  ቆላማ  በመሆኑ  ዝናብን  ጠብቆ  ሰብል  ማምረት  ስለማይታሰብ   ቤተሰባቸውን  ለማስተዳደር  ይቸገሩ  እንደነበር  አስታውሰዋል፡፡ በመንግስት ዘላቂ የልማት ፕሮጀክት በተደረገላቸው የሞተር ጀልባና የማስገሪያ መረብ ድጋፍ በዞኑ ባለው የተከዜ ሃይቅ ዓሳ ለማስገር 375 ሆነው ተደራጅተው በመስራት  ከአካባቢያቸው ሳይርቁ ሃብት መፍጠር እንደቻሉ ተናግረዋል። ማህበራቸው ዓሳ  ከማስገር  በተጨማሪ  ለአካባቢው  ማህበረሰብ  የጀልባ  ትራንስፖርት  አገልግሎት  በመስጠት አማራጭ የገቢ ምንጭ እንደሆናቸውም ጠቅሰዋል፡፡ ማህበራቸው  ዘንድሮ በ287  የላሜራና  የጣውላ  ጀልባዎች በመታገዝ  ባካሄደው ዓሳ የማስገር እንቅስቃሴ  ከ1ሚሊዮን 300ሺህ  ብር  በላይ  ገቢ በመሰብሰብ  አባላቱን ተጠቃሚ ማድረጉን አቶ  አምባየ ገልፀዋል፡፡ በግላቸውም ከዘርፉ በሚያገኙት ገቢ የቤተሰባቸውን ኑሮ ከማሻሻላቸው በላይ ከ70 ሺህ  ብር  በባንክ መቆጠብ ችለዋል። በዘርፉ ተሰማርተው ውጤታማ ቢሆኑም የመንገድ  መሰረተ  ልማትና  ቋሚ  የገበያ  ትስስር  ባለመኖሩ የዓሳ  ምርት  ለመሸጥ  ለዘጠኝ  ሰዓት  በጀልባ  በመጓዝ ጊዜና  ጉልበታቸውን  እንደሚያባክኑም ጠቁመዋል። በተከዜ ሃይቅ ከ2ሺህ 400  በላይ  አስጋሪዎች  በ183  ማህበራት ተደራጅተው  በዓሳ  ማስገር  ስራ  ተሰማርተው እንደሚገኙ የገለጹት ደግሞ በዞኑ እንስሳት  ሃብት  መምሪያ  የአሳ  ሃብት  ልማትና  ጥበቃ  ባለሙያ  አቶ  ዝናቡ  ፍቃዱ ናቸው። ማህበራቱ በሚያደርጉት የዓሳ ማስገር እንቅስቃሴም ባለፉት ዘጠኝ ወራት አንድ ሺህ 480 ቶን ዓሳ በማምረት ለአካባቢው ገበያና ለማዕከላዊ ገበያ አቅረበዋል። ባለሙያው እንዳሉት በተለይም አካባቢው ዝናብ አጠር ከመሆኑ ጋር በተያያዘ የዓሳ ማስገር ስራው ወጣቶችን ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል፤ ለማጠናከርም ለ10 ማህበራት 12 የሞተር ጀልባዎችና የቁሳቁስ  ድጋፍ  ተደርጓል። በዘላቂ ልማት ፕሮጀክትም  በዝቋላ፣ አበርገሌና  ሰሃላ  ወረዳዎች  ለሚገኙ አስጋሪዎች በ18 ሚሊየን  ብር  የዓሳ  ማቆያ   ሼድ ግንባታ ተከናውኗል፡፡ "ህብረተሰቡን  የዓሳ  ተጠቃሚ  ለማድረግም በሰቆጣና ኒሯቅ ከተማዎች የዓሳ  ሬስቶራንትና መሸጫ  ሱቆች በልማት ፕሮጀክቱ  ተገንብተው በቀጣይ  ዓመት ስራ ይጀምራሉ "ብለዋል ባለሙያው፡፡ የብሔረሰብ  አስተዳደሩ  መንገድና ትራንስፖርት መምሪያ ኃላፊ አቶ  ሰለሞን  እሸቱ  የዓሳ አስጋሪዎቹ  የመንገድ  መሰረተ  ልማት  ጥያቄ  ትክክለኛ  መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ሃይቁ  በሚያዋስናቸው  ወረዳዎች   በገጠር  ሁሉን  አቀፍ  መንገድ  ተደራሽነት  ፕሮግራም  ለማዳረስ  ጥረት  ቢደረግም  በቂ እንዳልሆነ አመልክተዋል፡፡ "በሶስቱም  ወረዳዎች  የመንገድ እና ትራንስፖርት  ተቋማት  ከሃይቁ  ጋር  የሚስተሳስራቸውን  የመንገድ  ጥናት  እንዲያቀርቡ በማድረግ  ለክልሉ  መንግስት  ጥያቄው  ቀርቦ  ምላሽ  እንዲሰጥበት  ይደረጋል" ብለዋል፡፡ በየብሄረሰብ  አስተዳደሩ  በየዓመቱ  በአማካይ   ከ2ሺህ 500  ቶን  በላይ  የዓሳ  ምርት  እንደሚሰበሰብ ተመልክቷል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም