የጤና ባለሙያዎች ሙያዊ ስነ-ምግባር ተላብሰው ለህሙማን አገልግሎት መስጠት አለባቸው

አዲስ አበባ  ግንቦት 17/2010 በጤናው ዘርፍ ያሉ ባለሙያዎች ለሙያውና ለተገልጋዮች ስነ-ምግባር በተላበሰና ህሙማንን በሚያከብር አግባብ ማገልገል እንደሚገባቸው ተገለጸ። 5ኛው የጤናው ዘርፍ የሰው ሃብት ልማት ፎረም " ብቃትና ሙያዊ ስነ-ምግባር የተላበሱ የጤናው ዘርፍ ሰራተኞች፣ ጥራት ላለው ሁሉን አቀፍ የጤና ገአግልግሎት" በሚል መሪ ሃሳብ እየተካሄደ ይገኛል። የጤና ጥበቃ ሚኒስቴሩ ዶክተር አሚር አማን በዚሁ ወቅት አንደገለጹት፤ በኢትዮጵያ የጤና አገልግሎት ሽፋኑን ተደራሽ ለማድረግ ዘርፈ ብዙ ስራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ። በዚህም ባለፉት 20 ዓመታት በተሰሩ ስራዎች ከ16ሺ በላይ የጤና ኬላዎች፣ 3ሺ700 የጤና ጣቢያዎችና 411 ሆስፒታሎች መገንባታቸው ገልጸዋል። በመሆኑም አገሪቱ በሁለተኛው እድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ የያዘችውን ለማሳካትም ያሉ የጤና ኬላዎች፣ የጤና ጣቢያዎችና ሆስፒታሎች መስራት የሚገባቸውን እንዲሰሩና መሟላት የሚገባቸውን ግብአቶችና የጤና ባመሉያዎችን እንዲሟሉ የማድረግ ስራ ትኩረት ይሰጠዋልም ብለዋል። "ለዚህም ደግሞ በተለይ በጤናው ዘርፍ ያሉ አካላት እውቀትና ክህሎት ይዘው ለሙያው ከፍተኛ ክብር በመስጠትና ለተገልጋዮች የሚገባውን አገልግሎት በማቅረብ በኩል ሚናቸው ከፍተኛ ሊሆን ይገባል" ነው ያሉት። ባለሙያዎች ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር በተያያዘ ህብረተሰቡ ለሚያነሳቸው ጥያቄዎች ተገቢውን መልስ በመስጠትም ከመማር ማስተማሩ ጀምሮ በስራ ላይ ባሉበት ሰዓትም ስነ-ምግባር በተላበሰና ህሙማንን በሚያከብር አግባብ ሊሆን እንደሚገባም አሳስበዋል። ሚኒስቴሩ በተለይ በሁለተኛው እድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ከተያዙ አጀንዳዎች መካከል አንዱ የጤና ባለሙያዎች ስነ-ምግባር የተላበሰና ህሙማንን የሚያከብር እንዲሆን እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል። በዚህም የሰው ኃብቱ በራሱ የሚተማመንና የአገልጋይነት መንፈስ የተሞላ እንዲሆን በማድረግ በኩልም በዘርፉ ካሉ አካላት ጋር በመወያየት የቅንጅት ስራ እንደሚሰራ አክለዋል። በፎረሙ የተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎችና ኮሌጆችን ጨምሮ በክልልና በዞን ያሉ በጤናው ዘርፍ የሚሰሩ የሙያ ማህበራት፣ ድርጅቶችና ሌሎችም አካላት እየተሳተፉ ሲሆን ለሚቀጥሉት ሶስት ቀናት የሚካሄድ ይሆናል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም