በዓይነቱ የመጀመሪያ የሆነ የእደ-ጥበብ ውጤቶች አውደ ርዕይ በአዲስ አበባ ሊካሄድ ነው

አዲስ አበባ ታህሳስ 15/2011 በዓይነቱ የመጀመሪያ የሆነ የእደ-ጥበብ ውጤቶች አውደ ርዕይ በአዲስ አበባ በተመረጡ የተለያዩ አደባባዮች ሊካሄድ ነው። የአዲስ አበባ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ባዘጋጀው በዚህ አውደ ርዕይ ከአስሩም ክፍለ ከተሞች የተወጣጡ 300 አምራቾች ይሳተፋሉ። አውደ ርዕዩ የተዘጋጀው በከተማዋ ያሉ የእደ ጥበበ አምራቾች ምርታቸውን ለማስተዋወቅና  ጠንካራ የገበያ ትስስር ለመፍጠር እንዲያስችላቸው ታስቦ መሆኑም ተመልክቷል። አገር በቀል እውቀትን በማስፋፋት ለትውልድ ማስረጽ ጭምር ዓላማን ያነገበው አውደ ርዕዩ ከነገ ታህሳስ 16 ቀን 2011 ጀምሮ ለአምስት ቀናት የሚቆይ ነው። የሚካሄደውም በሚኒሊክ አደባባይ፣ መገናኛ፣ ጦር ኃይሎች፣ አራት ኪሎና ለገሃር አካባቢ በተመረጡ ቦታዎች ላይ መሆኑን የከተማ አስተዳደሩ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ኃላፊ  አቶ ስዩም ተመስገን ዛሬ በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል። በአውደ ርዕዩ ባህላዊ አልባሳት፣ የሸክላ ምርቶች፣ በብርና በተለያዩ ግብአቶች የተሰሩ ጌጣጌጦች፣ የእንጨት ስራዎችና ባህላዊ የሙዚቃ መሳሪያዎች በአውደ ርዕዩ ከሚቀርቡት የእደ ጥበብ ውጤቶች መካከል ናቸው። አውደ ርዕዩ አዲስ አበባን የባህልና የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ የተጀመረውን ጥረት እንደሚያግዝም ምክትል ኃላፊው ገልፀዋል። አውደ ርዕዩ የአገር ውስጥ እደ ጥበብ ምርቶችን ከማስተዋወቅ ባሻገር  ህብረተሰቡ ዘንድም በቀላሉ እንዲደርሱ ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል ነው ያሉት። ቢሮው የባህል እሴቶችና ኢንዱስትሪ ልማተ ዳይሬክተር ወይዘሮ አዳነች ተመስገን  እንደተናገሩት  የአውደ ርእዩ ተሳታፊዎች ለተሳትፏቸው ምንም ዓይነት ክፍያ አይፈጽሙም፤ ድንኳን፣ ጠረጴዛ፣ ወንበር፣ የውኃና የመብራት አገልግሎት የሚቀርበው በቢሮው ነው። በተጨማሪም ከከተማዋ ፖሊስ፣ ደንብ ማስከበር፣ ትራፊክ ፖሊስና ከአካባቢ ጽዳትና ውበት ኤጀንሲ ጋር በጋራ ለመስራት የሚያሰችል ዝግጅቶች ተከናውኗል ሲሉ አከለዋል።                      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም