በቁልቢ ገብርዔል ንግሥ በዓል የምዕመናን ደህንነትን ለመጠበቅ ዝግጅት ተደርጓል -ፖሊስ

ሐረር ታህሳስ 15/2011 የፊታችን ዓርብ ለሚከበረው የቁልቢ  ገብርዔል ንግሥ በዓል የምዕመናንን ደህንነት ለመጠበቅ ዝግጅት መደረጉን የምስራቅ ሐረርጌ ዞን ፖሊስ መምሪያ አስታወቀ፡፡ የመምሪያው የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ዲቪዥን  ኃላፊ ኮማንደር ስዩም ደገፉ  ዛሬ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለጹት በዓሉን ለማክበር ከአገር ውስጥ፣ ከውጭ ኤርትራን ጨምሮ የሚመጡ ምዕመናንና ቱሪስቶችን ደህንነት ለመጠበቅ ዝግጅቱ ተጠናቋል። የበዓሉን አክባሪዎች ደህንነት ለማረጋገጥ የጥበቃ ሥራው በአጎራባች ክልሎች የጸጥታ ኃይሎችንና በመከላከያ ሠራዊት ጥምረት ከአዳማ ከተማ ጀምሮ እንደሚካሄድም ገልጸዋል። ከድሬዳዋና ከጅጅጋ ከተሞች አቅጣጫ ለሚመጡ ምዕመናን ደህንነታቸው ተጠብቆ በዓሉን እንዲያከብሩ ይደረጋል ብለዋል። በዓሉ በሚከበርበት ሥፍራ ፖሊስ የወንጀል ድርጊቶችን የሚፈጽሙ ግለሰቦችን ለመቆጣጠር ጊዜያዊ ፖሊስ ጣቢያዎች፣ዐቃቤ ሕግና ጊዜያዊ ፍርድ ቤት በማቋቋም ተጠርጣሪዎች ሲያዙ የምርመራ መዝገባቸው ተጣርቶ አፋጣኝ የፍርድ ሂደትን መሰረት ያደረገ ውሳኔ እንደሚሰጥም ተናግረዋል። ተጓዦች በሕገ ወጥ ድርጊት  የሚሰማሩ  ሰዎች  ሲያጋጥሟቸው በጊዜያዊ ፖሊስ ጣቢያ ስልክ ቁጥር 0253390355 ደውለው ጥቆማ በመስጠት ወንጀልን እንዲከላከሉ ኮማንደር ስዩም ጠይቀዋል። በሥፍራው የትራፊክ መጨናነቅ እንዳይፈጠር ከባድ የጭነት ተሽከርካሪዎች በበዓሉ ዋዜማና በዕለቱ መንገድ ላይ አቁሞ መሄድና መተላለፍ እንደማይችሉም ኃላፊው ተናግረዋል። በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ሐረርጌ ዞን ሜታ ወረዳ የሚገኘው የቁልቢ ገብርዔል በየዓመቱ በታኅሣሥና በሐምሌ ወራት በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ምዕመናን ያከብሩታል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም