ቀጥታ፡

ህዝቡ በትግራይ ለሚካሄዱ ውድድሮች ተጫዋቾችን ተቀብሎ ለማስተናገድ ዝግጁ ነው-ዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል

መቀሌ ታህሳስ 15/2011 የአማራ ክልል የእግር ኳስ ቡድን  በትግራይ ለሚያካሂደው ውድድር ህዝቡ በሰላም ተቀብሎ ለማስተናገድና ለመሸኘት ዝግጁ መሆኑን የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል አስታወቁ፡፡ ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ዛሬ በሰጡት መግለጫ ወንድም ከሆነው የአማራ ህዝብ አብራክ የወጡት ስፖርተኞችን  ያለ ፀጥታ ስጋት እንደሚያስተናግዷቸው ተናግረዋል። ከህዝብ ጋር ለማጋጨት አጀንዳ ያላቸው አንዳንድ ፖለቲከኞች ካለፈው ዓመት ጀምሮ በፈጠሩት ችግር የሁለቱም ክልሎች የእግር ኳስ ስፖርተኞች ውድድራቸውን በተለያዩ አካባቢዎች ሲያካሂዱ መቆየታቸውን አስታውሰዋል፡፡ ይህም ተወዳዳሪዎቹ ደጋፊያቸው በአቅራቢያቸው እንዳይኖር ከማድረጉም በላይ ላልተፈለገ ወጪ ሲዳረጉ እንደነበረም እንዲሁ። "የእግር ኳስ ተመልካቹ ደጋፊው በማይገኝበት በተለያዩ ቦታዎች ማካሄዱ ለስፖርተኛውም ጥሩ አይደለም፤ ለይስሙላ ብቻ ውድድር ማካሄድ ተገቢ አይደለም" ብለዋል፡፡ በሌላ ቦታ ተወዳደሩ እየተባለ አምና ችግር መፈጠሩን ያመለከቱት ዶክተር ደብረጽዮን ስፖርትና ፖለቲካ ሳይቀላቀሉ በየራሳቸው መድረክ ሊካሄዱ እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡ ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ እንዳሉት በስፖርት ጨዋታ የሚገኘው ውጤት በፀጋ ተቀብሎ እንግዳ ቡድኑን  በሰላም መሸኘት በክልሉ እየተጠናከረ መጥቷል፡፡ "የትግራይ ክልል የብሄር ግጭት የሚታይበት ሳይሆን ሰላም የሰፈነበትና  የማንኛውም ክልል ተወላጅ ያለስጋት የሚንቀሳቀስበት ነው" ብለዋል። የአማራ ክልል ስፖርተኞች ላይ የተለየ ችግር እንደማያጋጥም በቅርቡ ወደ ክልሉ ለመጣው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ልኡካን ቡድን የክልሉ መንግስት ያረጋገጠላቸው መሆኑን ምክትል ርእሰ መስተዳድሩ አመልክተዋል። የትግራይ የስፖርት ደጋፊዎች ስፖርታዊ ጨዋነት በተመላበት መንገድ ጨዋታውን በመከታተል  እንግዳ የመቀበል ባህሉንና ለሰላም ያለውን ፍላጎት ሊያሳይ እንደሚገባም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም