ኢጋድ በሶማሊያ ርእሰ መዲና ሞቃዲሾ የተፈፀመውን የቦምብ ጥቃት አወገዘ

102
አዲስ አባባ ታህሳስ 14/2011 የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን (ኢጋድ) በትናንትናው እለት በሶማሊያ ርእሰ መዲና ሞቃዲሾ የተፈፀመውን የቦምብ  ጥቃት አወገዘ። በሶማሊያ ፕሬዚዳንታዊ ቤተ-መንግስት አቅራቢያ በተቀነባበረው የቦንብ ጥቃት 20  የሚሆኑ ሰዎች ሲሞቱ ከ40 በላይ በሚሆኑት ላይ ደግሞ አካላዊ ጉዳት ደርሷል። ጥቃቱ የተፈፀመው አል-ሸባብ በሚሰኘው የሶማሊያ አሸባሪ ቡድን መሆኑን ሚዲያዎች ዘግበዋል። ኢጋድ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በላከው መግለጫ " በሲቪሎች፣ ወታደሮችና ጋዜጠኞች ላይ የተፈጸመው ግድያ በእጅጉ የሚያሳዝን ነው" ሲል ገልጿል። በጥቃቱ ሰለባ የሆኑት ዜጎች የአሸባሪውን ቡድን ለመመከት ያሳዩት ጀግንነትና የነፃነት ተጋድሎ ለዘመናት የሚዘከር ከመሆኑም በላይ ለመጪው ወጣት ትውልድም ከፍተኛ መነቃቃት የሚፈጥር ሆኖ እንደሚቀጥል የኢጋድ መግለጫ ጠቅሷል። " ከአይበገሬው የሶማሊያ ህዝብና ፌዴራል መንግስት ጎን በመሰለፍ ይህንን አረመኔያዊ የሽብር ተግባር ይኮንናል" ያለው ኢጋድ በጥቃቱ ሰለባ ለሆኑት ቤተሰቦችም መፅናናትን ተመኝቷል። ኢጋድ የሶማሊያ ፌዴራል መንግስት ሽብርተኝነትን ለመዋጋት የሚያደርገውን ጥረት በክልላዊና በአህጉራዊ የትብብር ስልቶች አማካኝነት የሚሰጠውን ድጋፍ እንደሚቀጥልም አረጋግጧል። ድርጊቱን አጥብቀው የኮነኑት የአገሪቱ ፕሬዚዳንት መሐመድ አብዱላሂ የሶማሊያን ህዝብ ሰላምና ብልፅግና ማረጋገጥ ይቻል ዘንድ ሽብርተኛ ቡድኑን ለማስወገድ የተጀመረው ዘመቻ ተጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉም ፕሬዚዳንቱ ተናግረዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም