ድጋፍ በማጣት ወደ ስራ ለመግባት መጉላላት እንደገጠማቸው ወጣቶች ገለጹ - ኢዜአ አማርኛ
ድጋፍ በማጣት ወደ ስራ ለመግባት መጉላላት እንደገጠማቸው ወጣቶች ገለጹ
ደብረማርቆስ ታህሳስ 14/2011 በጥቃቅን እና አነስተኛ ለመሰማራት ተደራጅተው ድጋፍ በማጣት ወደ ስራ ለመግባት መጎላላት እንደገጠማቸው በምስራቅ ጎጃም ዞን አስተያየታቸውን የሰጡ ወጣቶች ገለጹ፡፡ ከወጣቶቹ መካከል የደጀን ከተማ ነዋሪው ወጣት ታምሩ ልኡል ለኢዜአ እንዳለው ባለፈው ነሐሴ ወር ውስጥ ከአምስት ጓደኞቹ ጋር በከብት ማድለብ የስራ ዘርፍ ለመሰማራት ተደራጅተው ነበር፡፡ የብድር አገልግሎት ድጋፍ ባለማግኘታቸው ወደ ስራ መግባት እንዳልቻሉ የገለጸው ወጣቱ የሚመለከተው የመንግስት አካል እየተመላለሱ ችግሩችን ቢያመለክቱም ምላሽ አጥተው እየተጉላሉ መሆኑን ተናግሯል። ሲደራጁ የጠየቁትን 8መቶ ሺህ ብር ለማግኘት የሚጠበቅባቸውን 20 በመቶ መቆጠባቸውን ጠቁሟል። የማቻከል ወረዳ ቀበሌ ሁለት ነዋሪ ወጣት ስለእህት ሙላት በበኩሏ “ በጥቃቅን ተደራጅተን የመስሪያ ገንዘብ እና ቦታ አቅርቦት ችግር አጋጥሞናል” ብሏላች። እንደወጣቷ ገለጻ ወጣቷ ገለጻ በወተት ልማት ለመሰማራት ሶስት ሆነው ቢደራጁም የብድር አቅርቦት ባለማግኘታቸው ስራ መጀመር አልቻሉም ። ችግሩ ከነገ ዛሬ ይፈታል ብለው ከሚመለከተው መስሪያ ቤት በመመላለስ ጉልበትና ጊዜያቸውን እያባከኑ መጉላላት እንደገጠማቸው ተናግራለች፡፡ ከጓዳኞቹ ጋር በዶሮ እርባታ ለመሰማራት የተደረጁ ቢሆንም ብድርም ሆነ የመስሪያ ቦታ እንዳላገኙ የገለጸው ደግሞ በደብረማርቆስ ከተማ የቀበሌ ሰባት ነዋሪ ወጣት ይዘንጋው ዋሴ ነው፡፡ ከተደራጁ ከመስከረም ወር አንስቶ በተስፋ እየተጠባበቁ ቢቆዩም መልሳቸው በመደበኛ ብድር ወደስራ ግቡ የሚል መሆኑን ተናግረዋል። በመደበኛ ብድር የሚሰጠው ገንዘብ ከ50 ሺህ ብር በላይ ስለማይሆን ሊያሰራቸው እንደማይችል ጠቁሟል፡፡ በዞኑ ቴክኒክ እና ሙያ ኢንተርፕራይዝ መምሪያ የእቅድ ዝግጅትና ክትትል ቡድን መሪ አቶ ሞገስ ተመስገን እንዳሉት ወጣቶቹ ያቀረቡት ተዘዋዋሪ የብድር ገንዘብ ከክልል ባለመለቀቁ ምክንያት ቢዘገየም አሁን ከ77 ሚሊዮን ብር በላይ ደርሷቸዋል፡፡ ይህንንም ገንዘብ ለተጠቃሚዎች ለማስተላለፍ የስራ እድል ፈጠራ ግብረ ኃይል ተቋቁሞ እየሰራ መሆኑን አመልክተው በተጨማሪም በመጠነኛ የስራ ማስኬጃ ወደስራ ለመሰማራት ለሚፈልጉ ከመደበኛ ብድር እየተመቻቸላቸው መሆኑን አስረድተዋል፡፡ እስካሁንም ከመደበኛው ብድር ከ65ሚሊየን ብር በላይ ስራ ላይ መዋሉን ገልጸዋል፡፡ የመስሪያና የመሸጫ ቦታችን ለማመቻቸት በተደረገው ጥረት 79 ሼዶችን በመገንባት ለተጠቃሚ መተላለፋቸውን ጠቅሰዋል፡፡ ተጨማሪ የመስሪያ ቦታዎችን ለመገንባት እየተሰራ መሆኑንም ቡድን መሪው ጠቁመዋል፡፡ " በጀት ዓመቱ ከ110ሺህ በላይ ለሚሆኑ ወጣቶች የስራ እድል ለመፍጠር ታቅዶ እስከሁን 14ሺህ 315 ለሚሆኑ ስራ ፈላጊዎች የስራ እድል ተፈጥሯል " ብለዋል። በዞኑ ባለፈው ዓመት በተዘዋዋሪ ብድር የተመደበውን 351ሚሊየን ብር ከ91ሺህ በላይ ለሚሆኑ ስራ ፈላጊዎች በማከፋፈል ድጋፍ መደረጉም ተጠቁሟል።