ፋሲል ከተማ ድሬዳዋ ከተማን አንድ ለባዶ አሸነፈ

76
ሐረር ታህሳስ 13/2011 የኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ ሰባተኛ ሳምንት ሐረር ከተማ ላይ ጨዋታውን ያካሄደው ድሬዳዋ ከተማ በፋሲል ከተማ ተሸነፈ። በድሬዳዋ ስታድየም እድሳት ምክንያት ወደ ሐረር ተጉዞ ጨዋታውን ያካሄደው ድሬዳዋ ከተማ የተሸነፈው አንድ ለባዶ በሆነ ውጤት ነው። ከዕረፍት በፊት ጥሩ የተንቀሳቀሱት ፋሲል ከተማዎች በ21ኛው ደቂቃ የማሸነፊያዋን ግብ በ10 ቁጥሩ ሱራፌል ዳኛቸው አስቆጥረዋል። ከዕረፍት መልስም ሁለቱም ክለቦች ተመጣጣኝ እንቅስቃሴ ቢያደርጉም፤ ግብ ባለማስቆጠራቸው በዚሁ ውጤት ጨዋታው ተጠናቋል። የድሬዳዋ ከተማ ዋና አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ የተጨዋቾች ጉዳት ጨዋታው ላይ ተጽዕኖ እንደፈጠረባቸው ተናግረዋል። ውድድሩ ገና በመሆኑ መስተካከል ለሚገባቸውን ሥራዎች ትኩረት በመስጠት በቀጣይ አመርቂ ውጤት ለማስመዝገብ እንሰራለን ብለዋል። የፋሲል ከተማ ዋና አሰልጣኝ ውበቱ አባተ በበኩላቸው በቀጣይም በክለቡ ውስጥ የሚታዩትን ድክመቶች በማሻሻል ተፎካካሪነታቸውን እንደሚያጠናክሩ ተናግረዋል።በዛሬው ጨዋታ ባስመዘገቡት ውጤት እንደተደሱበት ገልጸዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም