ተመራቂ የጤና ባለሙያዎች ኀብረተሰቡን በቅንነት እንዲያገለግሉ የጤና ጥበቃ ሚኒስትሩ አስገነዘቡ - ኢዜአ አማርኛ
ተመራቂ የጤና ባለሙያዎች ኀብረተሰቡን በቅንነት እንዲያገለግሉ የጤና ጥበቃ ሚኒስትሩ አስገነዘቡ
ሀረር ታህሳስ 13/2011 ተመራቂ የጤና ባለሙያዎች ዘርፉ የሚጠይቀውን ሥነ- ምግባር በመላበስ ኅብረተሰቡን በቅንነት እንዲያገለግሉ የኢፌዲሪ ጤና ጥበቃ ሚኒስትር ዶክተር አሚር አማን አሳሰቡ። የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ የህክምና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የህክምና ዶክተሮችን ጨምሮ 220 የጤና ባለሞያዎችን ዛሬ አስመርቋል። ሚኒስትሩ ዶክተር አሚር በወቅቱ ባስተላለፉት መልዕክት "ተመራቂ የጤና ባለሙያዎች የሙያውን ሥነ- ምግባር በመላበስ ኅብረተሰቡን በቅንነትና በታማኝነት የማገልገል ኃላፊነት ተጥሎባችኋል" ብለዋል። "ከራስ ጥቅም ይልቅ ለወገን ቅድሚያ መስጠት፣ ብልሹ አሰራሮችን መከላከልና ውጤታማ ሥራን በማከናወን ለሌሎች አርአያ መሆን ይጠበቅባችኋል" ሲሉም አሳስበዋል። በሽታን አስቀድሞ መከላከል ላይ የተመሰረተውን የአገሪቱን የጤና ፖሊሲ የሚያጠናክሩ አገልግሎቶችን መስጠትና ጥናትና ምርምሮችን ማካሄድ እንዲሁም በእናቶችና ህጻናት ጤና ላይ ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንደሚገባም አስገንዝበዋል። የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድ አቶ ኦርዲን በድሪ ዩኒቨርሲቲው በጤናው ዘርፍ የባለሙያዎችን እጥረት ለማቃለል እያበረከተ ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል። ኮሌጁ በህክምና ሳይንስ ዘርፍ እያከናወነ ባለው የመማር፣ ማስተማርና ምርምር ሥራዎች በክልሉና አጎራባች አካባቢዎች እንዲሁም በአገር አቀፍ ደረጃ ዘርፉን የሚያጠናክሩ ተግባራት እያከናወነ መሆኑን ገልጸዋል። ዩኒቨርሲቲው የተማረ የሰው ኃይል የማፍራት ሥራው እንዲያጠናክር የክልሉ ህዝብና መንግሥት ድጋፍ እንደማይለየው ርዕሰ መስተዳድሩ አረጋግጠዋል። የዩኒቨርሲቲው በሐረር ከተማ በሚገኘው ኮሌጁ በመደበኛው የትምህርት መርሐ ግብር ካስመረቃቸው መካከል 173ቱ የህክምና ዶክተሮች መሆናቸውን የገለፁት ደግሞ የኮሌጁ ቺፍ ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር ዶክተር ያደታ ደሴ ናቸው። ቀሪዎቹ በመጀመሪያ ዲግሪ በነርስነት የሰለጠኑ ናቸው። ከአጠቃላይ ተመራቂዎች ውስጥ 38ቱ ሴቶች መሆናቸውንም ተናግረዋል። እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ ኮሌጁ በዚህ ዓመት በሕክምና ሳይንስ የቅድመ ምረቃ መርሐ ግብር በ11 ዘርፎች 2ሺህ 616 ተማሪዎች እያሰለጠነ ነው። በዕለቱ በከፍተኛ ማዕረግ የተመረቀችው ዶክተር ምህረት ለገሠ “የሙያ ሥነ- ምግባሩን በማክበር ኅብረተሰቡን በቅንነት ለማገልገል ተዘጋጅቻለሁ" ብላለች። የእናቶችንና የህጻናትን ሞት ለመቀነስ፣ የጤና አገልግሎቱን ለማሻሻልና በሽታን አስቀድሞ ለመከላከል የተየዘውን ጤና ልማት ግብ ለማሳካት የበኩሏን እንደምትወጣ ገልጻለች። ተመራቂ ዶክተር ቢሊሱማ ደገፉ በበኩሉ አገሪቱ የነደፈችውን የጤና ፖሊሲ ተግባራዊ ለማድረግ ኃላፊነቱን እንደሚወጣ አስታውቋል። የሐረማያ ዩኒቨርሲ ከአገሪቱ ቀደምት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አንዱ ቢሆንም፤ የሕክምና ዶክተሮች ሲያስመረቅ የአሁኑ ለሰድስተኛ ጊዜ ነው።