በታላቁ ህዳሴ ግድብ የጎዳና ላይ ሩጫ ከ500 ሺህ በላይ ሰዎች ይሳተፋሉ - ኢዜአ አማርኛ
በታላቁ ህዳሴ ግድብ የጎዳና ላይ ሩጫ ከ500 ሺህ በላይ ሰዎች ይሳተፋሉ
አዲስ አበባ ግንቦት 17/2010 የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የሰባት ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ ከ 500 ሺህ በላይ ሰዎች ይሳተፋሉ። የግድቡ ግንባታ የተጀመረበትን ሰባተኛ ዓመት አስመልክቶ ከነገ በስቲያ በአገር አቀፍ ደረጃ የሚካሄደው ሩጫ "ስለ ዓባይ እሮጣለሁ" በሚል መሪ ሀሳብ ይከናወናል። ሩጫውን የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ህዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት፣ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን፣ የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴርና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በጋራ አዘጋጅተውታል። የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሩጫ አቢይ ኮሚቴ አባልና የቴክኒክ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ዳንኤል ዳርጌ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ከ100 በላይ በሚሆኑ ከተሞች በሚከናወነው ሩጫ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ህዝብ ይሳተፋል። ለሩጫው 250 ሺህ ካናቴራ ለሽያጭ የተዘጋጀ ሲሆን ከሽያጩ 25 ሚሊዮን ብር ለመሰብሰብ መታቀዱን ጠቅሰዋል። ከተሳታፊው ቁጥር አንጻር ያለው የሩጫ ካናቴራ በቂ ባለመሆኑ መግዛት ያልቻሉ የህብረተሰብ ክፍሎችም በሩጫው መሳተፍ እንደሚችሉ ተናግረዋል። ሩጫው በሁሉም ቦታዎች ከንጋቱ 12 ሰአት ከ30 ደቂቃ እንደሚጀመር የገለጹት አቶ ዳንኤል በዚህ ሩጫ ላይ 90 ሺህ የሚሆኑ የአዲስ አበባ ነዋሪዎችም እንደሚሳተፉ ገልጸዋል። በአዲስ አበባ የሚካሄደው ውድድር መነሻውን መስቀል አደባባይ አድርጎ፣ በሜክሲኮ ቡናና ሻይ፣ በገነት ሆቴል ቄራ - ቄራ መገንጠያ በጎተራ ማሳላጫ አድርጎ መድረሻው መስቀል አደባባይ እንደሆነ ታውቋል። በመዲናዋ በሚካሄደው ውድድር የድንገተኛ አደጋ የህክምና ባለሙያዎች መኖራቸውንና ለህክምና እርዳታ አምቡላንሶች እንደተዘጋጁም አመልክተዋል። ሩጫው በሰላም እንዲጠናቀቅ ከጸጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት እንደተካሄደም አንስተዋል። ከገቢ ማሰባሰብ ባሻገር ሩጫው ህብረተሰቡ ስለ ህዳሴው ግድብ ንቅናቄ መፍጠርና ግድቡ የቀን ተቀን አጀንዳ አድርጎ እንዲንቀሳቀስ አላማ ያደረገ መሆኑንም ተናግረዋል። ከዚህ በፊት በ2005 እና በ2009 ዓ.ም በተካሄዱ ተመሳሳይ ሁለት ውድድሮች በአጠቃላይ ከ760 ሺህ በላይ ሰዎች መሳተፋቸውን አውስተዋል። የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሩጫ በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና እንዲያገኝና እንዲመዘገብ ጥረት እየተደረገ መሆኑንም አቶ ዳንኤል ጠቁመዋል። በአዲስ አበባው ውድድር በሁለቱም ጾታዎች ከአንድ እስከ ሶስት ለሚወጡ አትሌቶች የሜዳሊያ ሽልማት እንደሚበረከትና በክልሎች በሚካሄዱት ሩጫዎች ቦንድና ሌሎች ልዩ ሽልማቶች እንደተዘጋጁም አክለዋል። የግድቡ ግንባታ ሙሉ በሙሉ እስኪጠናቀቅ ህብረተሰቡ የጀመረውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል አቶ ዳንኤል ጥሪያቸውን አቅርበዋል። የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ በ2004 ዓ.ም የተጀመረ ሲሆን እስካሁን ባለው ሁኔታ የግድቡ ግንባታ ከ64 በመቶ በላይ መጠናቀቁን ከታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ህዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።