የኢትዮጵያ የተቋማት አደረጃጀት ሕብረ ብሔራዊነትን ማዕከል ያደረገ ነው - ረዳት ፕሮፌሰር ዘሪሁን - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የተቋማት አደረጃጀት ሕብረ ብሔራዊነትን ማዕከል ያደረገ ነው - ረዳት ፕሮፌሰር ዘሪሁን
አዲስ አበባ ታህሳስ 13/2011 በኢትዮጵያ የተቋማት አደረጃጀት ሕብረ ብሔራዊነትን ማዕከል ያደረገ መሆኑን በሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርስቲ የህግ መምህር የሆኑት ረዳት ፕሮፌሰር ዘሪሁን ይመር ገለፁ። የፌዴሬሽን ምክር ቤት በማንነት ጥያቄ አፈታት ላይ ያተኮረ ውይይት በአዳማ እያካሄደ ነው። የውይይት መነሻ ፅሁፍ ያቀረቡት ረዳት ፕሮፌሰሩ እንዳሉት የኢትዮጵያ የፌዴራሊዝም ሥርዓት ከነችግሮቹም ቢሆን ለዜጎች የማንነት ጥያቄ ምላሽ ሰጥቷል። ሕገ መንግሥቱ ከፀደቀ በኋላ 24 በሚሆኑ ቋንቋዎች ህፃናት በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው እንዲማሩ መደረጉን ጠቅሰዋል። የፌዴሬሽን ምክር ቤትን ጨምሮ በርካታ የመንግሥት ተቋማትም የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦችን ተዋፅኦ ባካተተ መልኩ ተደራጅተዋል። ብሔር፣ ቋንቋ፣ ማንነት፣ ታሪካዊ አመጣጥ፣ ማህበራዊ መስተጋብር የተካተቱበት ሕብረ ብሔራዊ አደረጃጀት እንደሆነም ጠቁመዋል። በዜጎች መካከል መቀራረብና መቻቻል እንዲጎለብት ለማድረግ ሕብረ ብሔራዊ አደረጃጀት መፍጠር ተገቢ መሆኑንም ነው የተናገሩት። በቅርቡ የመከላከያ ሠራዊትን ጨምሮ በሌሎች ተቋማት የሚደረገው የአደረጃጀትና የአወቃቀር ለውጥ ሕብረ ብሔራዊነቱን የበለጠ እንደሚያጎለብተውም ነው ረዳት ፕሮፌሰሩ ያብራሩት። ይሁን እንጂ ከፌዴራሊዝም ጋር በተያያዘ የሚነሱ የማንነት ጥያቄዎች በወቅቱ ምላሽ ሊሰጥባቸው እንደሚገባ አስገንዝበዋል።