ቀጥታ፡

ምክር ቤቱ በሶስት ረቂቅ አዋጆችና አንድ ፖሊሲ ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳለፈ

አዲስ አበባ ታህሳስ 13/2011 የሚኒስትሮች ምክር ቤት በዛሬ መደበኛ ስብሰባው በሶስት ረቂቅ አዋጆችና አንድ ፖሊሲ ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳለፈ። ምክር ቤቱ ከተወያየባቸው ጉዳዮች መካከል የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎትን እንደገና ለማቋቋም የወጣው ረቂቅ አዋጅ አንዱ ነው። የኢትዮጵያ ስፔስ ፓሊሲ፣ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች እና የሕገ መንግስትና ፌዴራሊዝም አስተምህሮ ማዕከልን ለማቋቋም የወጡት ረቂቅ አዋጆችም ምክር ቤቱ ተወያይቶ ውሳኔ ያሳለፈባቸው ናቸው። ምክር ቤቱ በቅድሚያ የተወያየበት የኢትዮጵያ ስፔስ ፓሊሲ ነው። ፖሊሲው ስፔስ ከአገሪቱ ኢኮኖሚያዊ መዋቅራዊ ለውጥ የማምጣት አቅጣጫ ጋር ተጣጥሞ በሂደት እንደ አንድ የኢንዱስትሪ ዘርፍ የአገሪቱን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ አስፈላጊ መሆኑ ታምኖበታል። በመሆኑም ምክር ቤቱ በቀረበው ረቂቅ ላይ ተወያይቶና ማስተካከያዎችን አክሎበት ሥራ ላይ እንዲውል ወስኗል። የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎትን እንደገና ለማቋቋም የወጣውን ረቂቀ አዋጅ በተመለከተም እንደ አገር የዜና አገልግሎቱ የተረጋገጠ መረጃ ለመስጠት ተቋማዊ የአሰራር ነፃነት እንዲኖረው አስፈላጊ መሆኑ ታምኖበታል። በመሆኑም የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎትን እንደገና ለማቋቋም ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጅቶ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ውሳኔ ቀርቧል። ምክር ቤቱም በረቂቅ አዋጁ ላይ በዝርዝር ተወያይቶ ማሻሻያዎችን በማካተት ይፀድቅ ዘንድ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ ወስኗል። የሕገ መንግስትና ፌዴራሊዝም አስተምህሮ ማዕከልን ለማቋቋም የወጣው ረቂቅ አዋጅም የዜጎችን የህገ መንግስትና የፌዴራሊዝም ግንዛቤ የሚያሰፋ፣ የመቻቻል ባህልን ለማጎልበትና አገራዊ እሴት ለማዳበር ያለው ሚና ከፍተኛ ነው። ምክር ቤቱም በዚህ ረቂቅ አዋጅ ላይ በዝርዝር ከተወያየ በኋላ አንዳንድ ማሻሻያዎችን በማካተት እንዲጸድቅ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ ወስኗል። በመጨረሻም የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ረቂቅ አዋጅ የዜጎችን ለህጋዊ ዓላማ የመደራጀት መብት ለማረጋገጥ የሚጠቅም በመሆኑ ምክር ቤቱ በቀረበው ረቂቅ አዋጅ ላይ በዝርዝር ተወያይቶበታል። በረቂቅ አዋጁ ላይ አንዳንድ ማሻሻያዎችን በማካተትም ይፀድቅ ዘንድ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ ወስኗል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም