ቀጥታ፡

ችሎቱ በኮሎኔል ጉደታ ኦላና እና በገመቹ ጫላ ላይ የጊዜ ቀጠሮ ሰጠ

አዲስ አበባ ታህሳስ 12/2011 ችሎቱ በቀድሞው የኢትዮ ቴሌኮም የሴኪዩሪቲ ዲቪዥን ሃላፊ ኮሎኔል ጉደታ ኦላና እና በሃሰተኛ የገንዘብ ቼክ ከባንክ ገንዘብ ሲያወጡ በተያዙት አቶ ገመቹ ጫላ ላይ የተጨማሪ የጊዜ ቀጠሮ ሰጠ። ተጠርጣሪው ግለሰብ ኮሎኔል ጉደታ ኦላና ከአንድ ወር በፊት በብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን የስራ ኃላፊዎች ላይ ምርመራ በሚያደርጉ የዐቃቤ ህግና ፌዴራል ፖሊስ አባላት ላይ ዛቻና ማስፈራት በማድረግ ምርመራ በማደናቀፍ ድርጊት ነበር የተያዙት። በምርመራ ሂደት ግን ፖሊስ ''ከገቢያቸው በላይ ምንጩ ያልታወቀ ሀብት በቤተሰባቸው ስም አካብተዋል፣ በሙስና ያገኙትን ገንዘብም ሕጋዊ በማድረግ ወንጀል ጠርጥሪያቸዋለሁ'' በሚል ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ጠይቆ ተፈቅዶለት ነበር። በተፈቀደለት ቀናትም ያከናወናቸውን ስራዎች ለፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 10ኛ ወንጀል ችሎት ዛሬ አስረድቷል። በቀጣይም ከባንኮች፣ ከሰነዶች ማረጋገጫና ከተለያዩ ክፍለ ለከተሞች በሃብት ማጣራት ላይ የጠየቅናቸውን የሰነድ ማስረጃዎች ለመቀበል፣ የተጠርጣሪን ቃል መቀበልና ግለሰቡ ጋር ቅርበት ካላቸው ሰዎች የምስክርነት ቃል መቀበል ስራዎች እንደሚቀሩት አመልክቷል። በዚህም ተጨማሪ የ14 ቀናት የጊዜ ቀጠሮ እንዲሰጠውና ተጠርጣሪ በዋስ ቢወጡ ምርመራ ሊያደናቅፉ ስለሚችሉ የዋስትና ጥያቄያቸው ውደቅ እንዲደረግ ጠይቋል። ተጠርጣሪ ኮሎኔል ጉደታ በጠበቃቸው በኩል እንዳስረዱት፤ ከተያዙ አንድ ወር ከሳምንት እንደሆናቸው ገልጸው፣ ፖሊስ ምርመራን በማደናቀፍ ወንጀል ድርጊት ቢያስራቸውም አዳዲስ ጉዳይ እያመጣ ተጨማሪ ጊዜ መጠየቅ አግባብ እንዳልሆነ ገልጸዋል። ተጠርጣሪ ምስጉን ሰራተኛ መሆናቸውን ገልጸው፣ በዋስ ቢወጡ ለፖሊስ አስፈላጊውን ማስረጃ ለመስጠት መተባበር እንጂ ምርመራ የማደናቀፍ ስብዕና ያላቸው ሰው አለመሆናችውን አስረድተዋል። ግራ ቀኙን ክርክር የተመለከተው ችሎቱ በተጠርጣሪ ላይ ፖሊስ ከጠየቀው 14 ቀናት ውስጥ ሰባት ቀናት በመፍቀድ፣ ለታኅሳስ 19 ቀን 2011 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል። በሌላ በኩል ችሎቱ  በተጭበረበረ የአንበሳ አውቶብስ አገልግሎት ቼክ ሀያ ሁለት አካባቢ በሚገኘው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 14 ሚሊዮን ብር በላይ ወደ ባንክ ሂሳቡ ለማዛወር ሲሉ በቁጥጥር ስር በዋሉት በአቶ ገመቹ ጫላ፣ ሃሰተኛ ቼክና መታወቂያ የሰጡ ግለሰብ እንዲሁም ከባንክ የወጣውን ብር ለመውሰድ መኪና ይዘው የነበሩ 3ኛ ተጠርጣሪን ጉዳይ ተመልክቷል። መርማሪ ፖሊስ በጠርጣሪዎች ላይ የምስክር ቃል መቀበል፣ የሰነድ ማስረጃ ማሰባሰቡና ሌሎች ስራዎችን ማከናወኑን ገልጾ፣ በቀጣይ ቀሪ ስራዎችን ለማከናወን ተጨማሪ ጊዜ እንዲፈቀድለት ጠይቋል። መርማሪ ቡድኑ ተጠርጣሪው በተለይም በንፋስ ስልክና አቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተሞች በሚገኙ ስድስት ወረዳዎች አቶ ገመቹ ጫላ በሃሰተኛ ቼክና የመታወቂያ ስሞች በመጠቀም ሌሎች የማጭበርበር ወንጀሎች ፈጽመዋል በሚል ጠርጥሮ ምርመራ እያደረገ መሆኑን ገልጿል። በተጠርጣሪ መታወቂያ ሌሎች ስሞችም ስላሉ የተጠርጣሪ እውነተኛ ስም አቶ ገመቹ ጫላ መሆን አለመሆኑንም አላረጋገጥኩም ብሏል። የተጠርጣሪዎችን ተከላካይ ጠበቆችና የመርማሪ ፖሊስን ክርክር ያደመጠው ችሎቱ በአንደኛ ተጠርጣሪ ገመቹ ጫላ ላይ የ14 ቀናት፣ በቀሪ ሁለት ተጠርጣሪዎች ላይ ደግሞ የ9 ቀናት ተጨማሪ ምርመራ ጊዜ ፈቅዷል። በዚህም አንደኛ ተጠርጣሪ ለታኅሳስ 26፣ 2ኛ እና 3ኛ ተጠርጣሪዎች ደግሞ ለታኅሳስ 22 ቀን 2011 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል። ከሜቴክ የስራ ኃላፊዎች ጋር በመመሳጠር 11 ሺ የአሜሪካን ዶላርና ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ አላግባብ በመቀበል በተጠረጠረችው ጋዜጠኛ ፍፁም የሺጥላ ላይ ደግሞ ችሎቱ በ50 ሺህ ብር ዋስ ጉዳይዋን በውጭ ሆና እንድትከታተል ፈቅዷል። የተጨማሪ 14 ቀናት የጊዜ ቀጠሮ ጥያቄው ውድቅ የተደረገበት መርማሪ ፖሊስ በበኩሉ ለተጠርጣሪዋ ላይ የተሰጠውን የዋስትና መብት ተገቢ አይደለም በሚል ይግባኝ ጠይቋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም