ቀጥታ፡

በአሜሪካ መንግስት ድጋፍ በ1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ዶላር ወጪ በአማራ ክልል የተገነባ ጤና ጣቢያ ተመረቀ

አዲስ አበባ ግንቦት 17/2010 የአሜሪካ መንግስት የልማት ተራድኦ ድርጅት (USAID) በአማራ ክልል ምዕራብ ጎጃም ዞን በአንድ ነጥብ ሶስት ሚሊዮን ዶላር ወጪ ያስገነባው  የቁኒ ጤና ጣቢያ ዛሬ ተመረቀ። የግንባታው ወጭ የተሸፈነው በአሜሪካ መንግስት የልማት ተራድኦ ድርጅት የኢትዮጵያ የጤና መሰረተ ልማት ፕሮግራም ነው። ጤና ጣቢያው በቁኒና በዙሪያዋ ላሉ ከ25 ሺህ በላይ ነዋሪዎች የህክምና አገልግሎቶችን የሚሰጥ ሲሆን በተለይ  የህጻናት ክትባት፣ የወሊድ ክትትል፣ የኤች.አይ.ቪ/ኤድስ ክትትልና ምክር አገልግሎት መስጠት የሚችል ነው። በኢትዮጵያ የአሜሪካ ኤምባሲ ለኢዜአ በላከው መግለጫ እንዳመለከተው፤ ጠንካራ የትምህርትና የቢዝነስ ተቋማት ቢፈጠሩም ያለ ጤናማ ማህበረሰብ ለውጥ አይመጣም። የአሜሪካ መንግስት የልማት ተራድኦ ድርጅት ለጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ቃል በገባው መሰረት የአገሪቱን የኅብረተሰብ ጤናን ለማሳደግ አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል። የቁኒ ጤና ጣቢያ ለአካባቢው ማህበረሰብ በቂ አገልግሎት መስጠት እንዲችል መንግስት የኤሌክትሪክ ሃይልና የህክምና መገልገያ ግብዓት ማቅረብ ይኖርበታል ተብሏል። የአሜሪካ መንግስት የልማት ተራድኦ ድርጅት ባለፉት 10 ዓመታት 22 ጤና ጣቢያዎችን፣ 10 የመድሃኒት ማከማቻ መደብሮችን ገንብቷል። በተጨማሪም በአሁኑ ወቅት በአንድ ወር ውስጥ ግንባታው ተጠናቆ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የሚረከበው የብሄራዊ የደም ባንክ ማዕከል ግንባታ እየተከናወነ ነው። የአሜሪካ መንግስት ለኢትዮጵያ የጤና ዘርፍ እድገት ግንባር ቀደም አጋር ሲሆን ለኤች.አይ.ቪ/ኤድስ፣ የወባ ህክምና፣ ለእናቶችና ህፃናት ጤና፣ ለሳንባ ነቀርሳ እንዲሁም ለውሃና ለግል ንጽህና የሚውል በየአመቱ 200 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ያደርጋል። የአሜሪካ መንግስት ባለፉት አምስት አመታት ለኢትዮጵያ የልማትና ሰብአዊ ድጋፍ የሚውል 3 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ አድርጓል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም