ቀጥታ፡

የፌደራል ተቋማት በፓርኩ ብዝሃ ሕይወት ላይ እየደረሰ ያለውን ችግር ለመከላከል ትኩረት እንደሚሰጡ ገለጹ

ጋምቤላ ታህሳስ 12/2011 በጋምቤላ ብሔራዊ ፓርክ ብዝሃ ሕይወት ላይ እየደረሰ ያለውን ችግር ለመከላከል የፌደራል ተቋማት ትኩረት እንደሚሰጡ ገለጹ፡፡ ፓርኩን ከችግር ለማውጣት ከተለያዩ አካላት ጋር የተደረገው  ውይይት ባለ8 ነጥብ የአቋም መግለጫ በማውጣት ተጠናቋል፡፡ በፓርኩ ብዝሃ ሕይወት ላይ እየደረሰ ያለውን ችግር በመከላከል ፓርኩን የጎብኚዎች መዳረሻ ለማድረግ ባለድርሻ አካላት በትኩረት እንደሚሰሩ አስታውቀዋል፡፡ ፓርኩ የእንስሳትና የእፅዋት ብዝሃ ህይወት ያቀፈ እንደመሆኑ ከገጠሙት ችግሮች በመታደግ የክልሉን ብሎም የአገሪቱን የኢኮቱሪዝም ዘርፍ ለማሳደግ እንደሚሰሩ ተሳታፊዎቹ ተናግረዋል፡፡ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የማህበራዊ ጉዳይ ዳይሬክተር አቶ በቀለ መንገሻ እንደተናገሩት ፓርኩን ከችግሮቹ ለማውጣት በቅንጅት  መሰራት እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡ በተለይም ፓርኩ በኢትዮጵያና ደቡብ ሱዳን ድንበር ላይ ስለሚገኝ ደህንነቱን ለማስጠበቅና የጸጥታ አካላት በጋራ መሥራት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል፡፡ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የውጭ ቱሪዝም ማስፋፊያ ባለሙያ አቶ ካህሳይ ጋይም በበኩላቸው ሚኒስቴሩ ፓርኩን ከችግር ለመታደግና የቱሪስቶች መዳረሻ ለማድረግ ይሰራል ብለዋል፡፡ ሚኒስቴሩ በፓርኩ ላይ ችግር እያደረሱ ያሉትን የፈላታ አርብቶ አደሮችን ወደ ፓርኩ እንዳይገቡ ለማድረግ በአገሮቹ መካከል ያለውን ግንኙነት በማጤን ምላሽ እንደሚሰጥ  ገልጸዋል፡፡ የአካባቢ፣ደንና አየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን አቶ ፍቅሩ አራጋው በበኩላቸው ኮሚሽኑ በክልሉ የሚታየው የደን ጭፍጨፋ ለእንስሳትም ሆነ ለአካባቢው ሥነ-ምህዳር እየፈጠረ ያለውን ችግር ለመፍታት እንደሚሰራ ገልጸዋል፡፡ በተለይም ኮሚሽኑ በተያዘው የበጀት ዓመት የደን ዓዋጅ በማውጣት ወደ ስራ ለመግባት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንና ይህንንም እስከ ቀበሌ ድረስ ተግባራዊ እንደሚደረግ ተናግረዋል፡፡ የደን ጭፍጨፋን ለመከላከልና የአካባቢውን ሥነ ምህዳር ለመጠበቅ ለኅብረተሰቡ የግንዛቤ ማሰጨበጫና ተዛማጅ ሥራዎችን በማከናወን የደን ጭፍጨፋን ለማስቀረት ይሰራል ብለዋል፡፡ የኢትዮጵያ ዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለሥልጣን ምክትል ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን መኮንን የአመራር አካላት የፓርኩን ህልውና ለመጠበቅ  ቁርጠኝነት ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የፈላታ አርብቶ አደሮችን ለመከላከል የሚደረገውን ጥረት ከፓርኩ ባለፈ ለአካባቢው ፀጥታም ችግር እንደሚሆንም ተናግረዋል፡፡ ባለሥልጣኑ የፓርኩን ችግሮች  ሙሉ በሙሉ እንዲፈታ የክልሉ ብሎም የፌደራል መንግሥት በጋራ እንዲረባረቡ ጠይቀዋል፡፡ የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር ተወካይ ዶክተር ሎው ኡቡፕ በበኩላቸው ለግል ጥቅማቸው ሲሉ ፓርኩን አደጋ የሚጥሉ የአመራር አካላት ድርጊት የሚፈጽሙ አመራሮችን የክልሉ መንግስት እንደማይታገሳቸው ተናግረዋል፡፡ የክልሉ መንግሥት የደን ጭፍጨፋና ህገ ወጥ የእንስሳት አደንን ለመከላከል በትኩረት እንደሚሰራም ገልጸዋል፡፡ በመሆኑም የክልሉ ሕዝብም ሆነ የሚመለከታቸው አካላት ከክልሉ መንግሥት ጎን ሆነው እንዲሰሩም ጥሪ አቅርበዋል፡፡ የጋምቤላ ብሔራዊ ፓርክ ከ46 ዓመታት በፊት የተቋቋመ ሲሆን፣ 69 የአጥቢ፣ 327 የአዕዋፍና 490 በላይ እፅዋት ዝርያዎች አሉት።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም