ቀጥታ፡

እሴት የማይጨምር የግብይት ሰንሰለት ችግር ለመፍታት የጋራ ርብርብ ያስፈልጋል

አዳማ ታህሳስ 12/2011 እሴት የማይጨምሩ የተንዛዙ ልማዳዊ የግብይት ሰንሰለቶች አምራቹን የማያበረታቱና ምርትና ምርታማነትን እንዳያድግ ተፅእኖ የሚፈጥሩ በመሆናቸው ችግሩን ለመፍታት የጋራ ርብርብ እንደሚያስፈልግ ተገለጸ። የግብይት ሰንሰለቱ ተዋናዮችና ሌሎች  ባለድርሻ አካላት የተሳተፉበት የአትክልትና ፍራፍሬ አምራች ህብረት ስራ ማህበራት እና የሸማቾች ተቋማት የገበያ ትስሰር መድረክ ዛሬ በአዳማ ከተማ ተካሄዷል። የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ዓይናለም ንጉሴ በምክክር መድረኩ እንደተናገሩት አሁን ባለው ገበያ ከአምራቹ ይልቅ ከፍተኛ ተጠቃሚዎች የሚሆኑት በእሴት ሰንሰለቱ ላይ ዋነኛ ተዋናዮች የሆኑት ደላሎች ፣ ጅምላ ነጋዴዎችና ቸርቻሪዎች ናቸው ። "ይህ  እሴት የማይጨምር የግብይት ሰንሰለት አምራቹ አርሶ አደር እንዳይበረታታ ፣ ምርትና ምርታማነቱ በዘላቂነት እንዳይሻሻልና ለሀገር ውስጥና ለውጭ ገበያ በቂ ምርት በጥራት እንዳይቀርብ  እንቅፋት  በመሆኑ ችግሩ በሁሉም አካላት ርብርብ በፍጥነት ሊቀረፍ ይገባል" ብለዋል ። በሀገሪቱ እየታየ ያለው የእድገትና የብልፅግና ጉዞ ስኬት ውስጥ የህብረት ስራ ማህበራት ሚና ከፍተኛ መሆኑን ያመለከቱት ሚኒስትር ዴኤታዋ  በተለይም ግብርናውን ለማዘመን  አርሶ አደሩ የቴክኖሎጂ ተጠቃሚ እንዲሆንና ምርታማነቱን በዘላቂነት እንዲያሳድግ ወሳኝ ሚና እንዳለው ገልጸዋል። የህብረት ስራ ማህበራት ዋና ተልዕኳቸው ምርቶችን በተለይ ደግሞ አትክልትና ፍራፍሬ ለሸማች ድርጅቶችና ተቋማት በማቅረብ ጤናማ የግብይት ትስስር እንዲፈጥሩ በማመቻቸት አምራቹንና ሸማቹን ተጠቃሚ ማድረግ በመሆኑ በግብይት ሰንሰለቱ ላይ የሚታዩ ክፍተቶች ማስተካከል እንደሚገባ አስገንዝበዋል ። የፌዴራል ህብረት ስራ ኤጀንሲ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ አብዲ ሙመድ በበኩላቸው በአትክልትና ፍራፍሬ ዘርፍ የሚታየውን  ረጅም   የግብይት ሰንሰለት ማጠር እንዳለበት አመልክተዋል። አቶ አብዲ እንዳሉት ዘላቂነት ያለው ጤናማ የገበያ ትስስር በመፍጠር የአምራቹንና ሸማቹን ህብረተሰብ ተጠቃሚነት  ለማረጋገጥ ሁሉንም ባለድርሻ አካላት የጋራ ግንዛቤ ይዘው በኃላፊነት መንፈስ ሊረባረቡ ይገባል። "ኤጀንሲው የህዝብን የልማት ጥያቄ በተደራጀ አቅም ለመመለስ የህብረት ስራ ማህበራትን የማደራጀት ፣ የማጠናከር ፣ የግብይት ትስስር በመፍጠር ፣ ቁጠባንና ኢንቨስትመንትን በማሳደግና የተለያዩ የአቅም ግንባታ ድጋፎች በማድረግ ተልዕኮውን በአግባቡ እየተወጣ ነው "ብለዋል፡፡ " የህብረት ስራ ማህበራት ጉዳይ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ  የ80 ሚሊዮን ሰዎች ጉዳይ ነው " ያሉት ደግሞ በኤጀንሲው የህብረት ስራ ግብይት ዳይሬክተር ወይዘሮ ይርጋለም እንየው ናቸው ። ዳይሬክተሯ ይህንኑ ያሉት በምክክር መድረኩ በአትክልትና ፍራፍሬ ግብይት ትስስር ላይ ያተኮረ የመነሻ ፅሁፍ ሲያቀርቡ ነው  ። በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ የትግበራ ዘመን ሶስተኛው ዓመት ላይ 19 ሚሊዮን 500 ሺህ  አባላት ያሏቸው  85 ሺህ 496 መሰረታዊ የህብረት ስራ ማህበራት በስራ ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል። አንድ አባል በትንሹ በአማካይ 4 የቤተሰብ ብዛት ቢኖረው እንኳን የህብረት ስራ ማህበራት ጉዳይ የ80 ሚሊዮን ሰዎች ጉዳይ መሆኑን በዝርዝር አስረድተዋል ። 22 ቢሊዮን 900 ሚሊዮን ብር ካፒታል የሚያንቀሳቅሱት እነዚህ ማህበራት የበለጠ እንዲጠናከሩ ማድረግ ሀገራዊ ጠቀሜታው የላቀ መሆኑን ገልፀዋል ። በተለይ በአትክልትና ፍራፍሬ ዘርፍ  ባለፈው ዓመት ለገበያ ከቀረበው 973 ሺህ 927 ሜትሪክ ቶን ምርት 52 ነጥብ 3 በመቶ በህብረት ስራ ማህበራት አማካኝነት መሆኑን ጠቁመዋል ። ሆኖም በተንዛዛና እሴት በማይጨምር የግብይት ሰንሰለት ምክንያት አምራቹም ሆነ ሸማቹ ተጠቃሚ እንዳልሆነ አመልክተዋል ። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አትክልትና ፍራፍሬ አምራቾችን ከዩንቨርሲቲዎች ፣ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ፣ ከሸማቾችና ከኢትፍሩት ጋር የገበያ ትስስር እንዲፈጥሩ በማድረግ አንፃራዊ መሻሻሎች ቢኖሩም የበለጠ መጠናከር እንዳለባቸው አሳስበዋል ። በመድረኩ የግብርና ፣ አርብቶ አደርና አካባቢ ጥበቃ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት ፣ የህብረት ስራ ማህበራት አመራሮች ፣ የክልልና የፌደራል የዘርፉ ኃላፊዎችና ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ተሳትፈዋል። እሴት የማይጨምር የግብይት ሰንሰለት ለማሳጠር በሚደረገው ጥረትም የበኩላቸውን እገዛ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን ተሳታፊዎቹ  ገልፀዋል ። የህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም   ለሸቀጦች ዋጋ መናር ምክንያት በሆኑ ደላሎች ፣ ዋጋን በምክር በሚወስኑ አድመኛ ነጋዴዎችና ያልተገባ ጥቅም ለማግበስበስ ሲሉ በሚተባበሩዋቸው የመንግስት ተቆጣጣሪ አካላት ላይ ተገቢ እርምጃ እንዲወሰድ ባለፈው ጥቅምት ወር አጋማሽ መጠየቁ ይታወሳል ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም