ቀጥታ፡

አምባሳደር ሉሊት ዘውዴ ለኮንጎ ሪፐብሊክ ፕሬዚዳንት ዴኒስ ሳሶ ኒጌሶ የሹመት ደብዳቤ አቀረቡ

አዲስ አበባ 12/2011 በኮንጎ ሪፐብሊክ የኢትዮጵያ ልዩ መልዕክተኛና ባለ ሙሉ ስልጣን አምባሳደር ሉሊት ዘውዴ የሹመት ደብዳቤያቸውን ለአገሪቱ ፕሬዚዳንት ዴኒስ ሳሶ ኒጌሶ  ታህሳስ 9 ቀን 2011 ዓ.ም  ማቅረባቸውን የውጭ ጉዳይ ሜኒስቴር ገለጸ። አምባሳደር ሉሊት የሁለቱን አገሮች ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ ማንኛውንም እንቅስቃሴ ከኮንጎ ሪፐብሊክ ጎን በመሆን የተቻለውን ሁሉ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል። የኢትዮጵያን ሁኔታ በቅርበት የሚከታተሉት የኮንጎ ሪፐብሊክ ፕሬዚዳንት ዴኒስ ሳሶ ኒጌሶ የኢትዮጵያ እድገት የሁሉም አፍሪካ እድገት መሆኑን ገልጸዋል። የኢትዮጵያ መንግስት ሴቶችን ወደ ውሳኔ ሰጪነት ኃላፊነት ማምጣቱ ተገቢ ርምጃ መሆኑን ተናግረዋል። በሁለቱ አገሮች መካከል የተፈረሙ ስምምነቶች ተግባራዊ እንዲደረጉ የጠየቁት ፕሬዝዳንቱ በአገራቸው ከፍተኛ ትኩረት የሚሰጠው የአየር ትራንስፖርት አገልግሎት ስምምነት እንደሆነ ጠቁመዋል። ኮንጎ ሪፐብሊክ የራሷ አየር መንገድ ለማቋቋም በምታደርገው እንቅስቃሴ የኢትዮጵያን ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው እንደሆነ መናገራቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለኢዜአ በላከው መግለጫ አመልክቷል። ፕሬዝዳንት ዴኒስ ሳሶ ኒጌሶ ኢትዮጵያ ትልቅ እና ለመላው አፍሪካ ተምሳሌት የሆነች ሀገር መሆኗን ገልጸው አገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር ያላት የረጅም ጊዜ ግንኙነት ይበልጥ እንዲያድግ በአምባሳደሯ የስራ ዘመን ድጋፋቸውን እንደሚያደርጉ አረጋግጠዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም