ቀጥታ፡

ከሥነ ምግባር፣ ከህሊናና ከሞራል አኳያ ግብር መክፈል የዜጎች ኩራት ነው - የሃይማኖት አባቶች

አዲስ አበባ ታህሳስ 12/2011 ከሥነ ምግባር፣ ከህሊናና ከሞራል አኳያ ግብር መክፈል የዜጎች ኩራት መሆኑን የሃይማኖት አባቶች ተናገሩ። ግብር መክፈል የውዴታ ግዴታ በመሆኑ በየቤተ-እምነታቸው ይህንኑ የሚያስገነዝብ ትምህርት እንደሚሰጡም አስታውቀዋል ። ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ ለአንድ ዓመት የሚካሄደውን የታክስ ንቅናቄ አገር አቀፍ መርሃ ግብር ዛሬ በይፋ አስጀምረዋል። "ግዴታዬን እወጣለሁ መብቴንም እጠይቃለሁ" በሚል መሪ ሃሳብ የሚካሄደውን የታክስ ንቅናቄ አገር አቀፍ መርሃ ግብር ያዘጋጀው የገቢዎች ሚኒስቴር ነው። በዚህ ልዩ መድረክ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ታድመዋል። የሃይማኖት አባቶች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ የተፎካካሪ ፓርቲዎች፣ የንግዱ ማህበረሰብ፣ የ1ኛና የ2ኛ ደረጃና የዩኒቨርሲቲዎች፣ የወጣቶችና ተማሪዎች፣ የመምህራን፣ የመንግሥት ሠራተኞችና የግብር አምባሳደሮች ተወካዮችም መልዕክት አስተላልፈዋል። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ፣ የእስልምና፣ የካቶሊክ፣ የፕሮስቴስታንትና የወንጌላዊያን ቤተክርስቲያናት ህብረትን የወከሉት የሃይማኖት አባቶች ከሥነ ምግባር፣ ከህሊናና ከሞራል አኳያ ግብር መክፈል የዜጎች ኩራት መሆኑን ነው የተናገሩት። አገር ያለግብር ስለማይገነባ ለህብረተሰቡ ግንዛቤ በማስጨበጥ አገራቸውን ከመቼውም ጊዜ በላይ ለማገልገልም ቃል ገብተዋል። 'በአገሪቱ ታማኝ ግብር ከፋዮች ነን' ያሉት የመንግሥት ሠራተኞች ተወካይም ሁሉም ዜጋ የእነርሱን አርአያ እንዲከተል ጠይቀዋል። የመንግሥት ሠራተኞች ግዴታችንን ስንወጣ 'በየደረጃው መብታችንም መከበር አለበት' ሲሉም አክለዋል። የንግዱ ማህበረሰብ ተወካይ በበኩላቸው ነግደን ከምናተርፈው፣ ሠርተን ከምናገኘው ገቢ ለመንግሥት የሚገባውን ግብር ለመክፈልና በህጋዊ ደረሰኝ ለመገበያየት ቃል እንገባለን፤ ግዴታችንንም በመወጣት መብታችንን እንጠይቃለን ብለዋል። ግብርን በወቅቱና ያለማጭበርበር መክፈል በሥነ ምግባር የታነፀ ትውልድ ለማፍራት ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የወጣቶችና የተማሪዎች ተወካይ ናቸው። የመምህራን ተወካይም ተማሪዎቻቸውን ግብር መክፈል ግዴታና ለአገር ልማትና አስተዋጽኦ እንዳለው በማስገንዘብና ምሩቃን ሥራ ፈጣሪ በመሆን አገራቸውን ለመጥቀም ግብር ከፋይ እንዲሆኑ ለማስቻል የድርሻቸውን እንደሚወጡ ነው የተናገሩት። በራስ ተነሳሽነት በተለያዩ የግብር ንቅናቄዎች የተሳተፉት የግብር አምባሳደሮች የዘመቻው ግንባር ቀደም በመሆን ሥራዎቻቸውን ሁሉ ከግብር ጋር በማስተሳሰር ለመስራት ቃል ገብተዋል። የተፎካካሪ ፓርቲዎች ወካዮችም አገሪቷ በለውጥ ሂደት ላይ በመሆኗ ሥርዓት ያለው የገቢ ግብር ወሳኝ በመሆኑ የንቅናቄውን መሳካት ከግብ ለማድረስ የድርሻቸውን እንደሚወጡ አስታውቀዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም