ቀጥታ፡

ባንኩ በወጪ ንግድ ዘርፍ ከ1 ነጥብ 4 ቢሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ ላስገኙ ላኪዎች እውቅና ሰጠ

አዲስ አበባ  ታህሳስ 12/2011 የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ2010 ዓ.ም የወጪ ንግድ አፈፃፀም ከ1 ነጥብ 4 ቢሊዮን ዶላር በላይ የምንዛሬ ገቢ ላስገኙ ላኪዎች እውቅና ሰጠ። ባንኩ  ለ182 ተቋማት በየደረጃው ከልዩ ሽልማት እስከ ምስክር ወረቀት ድረስ እውቅና ሰጥቷል። በዚሁ መሰረት ሶስት ተቋማት ልዩ ተሸላሚ ሲሆኑ አምስት የፕላቲንየም፣ 10 የወርቅ፣ 16 የብርና 28 የነሃስ ሽልማት ተበርክተዋ፤ 120 ተቋማት ደግሞ የምስክር ወረቀት ተቀብለዋል። እነዚህ በወጪ ንግድ የተሰማሩ ተቋማት ከባንኩ ጋር በመስራት ለአገሪቱ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ በማስገኘት አስተዋጽኦ ያበረከቱ ናቸው። የባንኩ የቦርድ ሰብሳቢ አቶ አህመድ አብተው በዚሁ ጊዜ ባስተላለፉት መልዕክት ዘርፉ የአገር ኢኮኖሚ ጤናማና የወደፊቱን የእድገት ደረጃ የሚወስን በመሆኑ በዚሁ ተሳትፈው የላቀ ውጤት ላስመዘገቡ እውቅና መስጠት ተገቢ መሆኑን ተናግረዋል። እውቅናው ዘርፉ ከዚህ በላቀ የወደፊት እድገቱን በሚያሳካ ደረጃ እንዲሄድና በቀጣይ ሁሉም ተሸላሚ የሚሆንበትን እድል እንደሚፈጥር ያላቸውን እምነትም አክለዋል። የባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ ባጫ ጊና በአገሪቱ ልማት የጎላ ሚና ያለውን ይህን ዘርፍ ለማበረታታ የተለያዩ ስራዎች እየተሰሩ ነው ብለዋል። ዘርፉን ለማሻሻል ችግሮችን በመለየትና ከባለድርሻ አካላት ግብዓት በማሰባሰብ መፍትሄ ለማበጀት እየተሰራ መሆኑንም ገልፀዋል። ባንኩ በወጪ ንግድ ዘርፍ የተሰማሩ ተቋማትን ውጤታማ ለማድረግ እንደሚሰራም ነው ያብራሩት። በትናንቱ የሽልማት ሥነ-ስርዓት ኢትዮ ቴሌኮም፣ የኤሌክትሪክ አገልግሎትና የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከተሸላሚ ተቋማት መካከል ነበሩ። የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከ20 ሚሊዮን በላይ ደንበኞች ያሉት ሲሆን በመላ አገሪቱ 1 ሺህ 320 ቅርንጫፎች አሉት።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም