ቀጥታ፡

ባለሥልጣኑ ፓርኩ እየደረሰበት ካለው ችግር ለመታደግ ባለድርሻ አካላት ሚናቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቀረበ

ጋምቤላ ታህሳስ 12/2011 የጋምቤላ ብሔራዊ ፓርክ እየደረሰበት ካለው ችግር ለመታደግ በሚደረገው ጥረት ባለድርሻ አካላት ሚናቸውን እንዲወጣ የኢትዮጵያ ዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለሥልጣን ጥሪ አቀረበ። ''እኔ ለተፈጥሮ ሀብቴ አምባሳደር ነኝ!'' በሚል መሪ ቃል በፓርኩ ላይ እየደረሰ ያለውን ችግር ለመከላከል ባለድርሻ አካላት የተሳተፉበት የንቅናቄ መድረክ ትናንት በጋምቤላ ከተማ ተካሄዷል። የባለሥልጣኑ ምክትል ዳሬክተር አቶ ሰለሞን መኮንን በመድረኩ ላይ እንደገለጹት በድንበር ዘለል አርብቶ አደሮች፣ በሕገ ወጥ ሰፋሪዎችና በሌሎች ችግሮች በብዝሃ ሕይወት ላይ ጉዳት እየደረሰ ነው። በተለይም ድንበር ዘለል የፈላታ አርብቶ አደሮች የቀንድ ከብቶቻቸውን ይዘው ወደ ፓርኩ በመግባት ልቅ ግጦሽ በማካሄድ በብዝሃ ሀብቱ ላይ ጥፋት እያደረሱ ነው ብለዋል። በተጨማሪም በሕገ ወጥ አደን፣ በሰፈራ፣ በእርሻ ሥራ፣ በደን ጭፍጨፋ የፓርኩ መጠለያ እንዲመናመንና የዱር እንስሳቱ በመሰደድ ላይ እንደሚገኙም ተናግረዋል። ባለሥልጣኑ ችግሩን ለመከላከል ጥረት ቢያደርግም  ከአቅም በላይ እየሆነበት ይገኛል ብለዋል። በመሆኑም የአካባቢው ማህበረሰብ፣ በየደረጃው የሚገኙ የአመራር፣ የጸጥታና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ፓርኩን ከጥፋት ለመታደግ ሚናቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል። መድረኩ ባለድርሻ አካላት በፓርኩ ላይ እየደረሰ ያለውን ጉዳት ተገንዘበው አጋርነታቸውን ለመወጣት እንደሚያስችላቸው ምክትል ዳይሬክተሩ ተናግረዋል። የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ተወካይ ዶክተር ሎው ኡቡፕ በመድረኩ ላይ እንደተናገሩት በፓርኩ የሚገኙ እምቅ የዱር እንስሳትና ሌሎች የብዝሃ ሕይወት ተጠብቀው ለትውልድ እንዲተላለፉ የሁሉም አካላት በልማትና ጥበቃ ሚናውን እንዲወጣ ጠይቀዋል። የክልሉ መንግሥት የፓርኩን ብዝሃ ህይወት ለመጠበቅና ለማልማት በሚደረገው ጥረት በሁሉም የአስተዳደር እርከኖችን የሚገኙ አካላት በማስተባበር ድጋፍ ለመስጠት ዝግጁ መሆኑን ተናግረዋል። ከመድረኩ ተሳተፊዎች መካከል አቶ ብሊሚ ኡዶል በሰጡት አስተያየት የፈላታ አርብቶ አደሮች በፓርኩ ብቻ ሳይሆን ሌሎች ድንበር ዘለል የቀንድ ከብት በሽታዎችን ሊያስከትሉ ይችላሉ ብለዋል። አርብቶ አደሮቹ ከአካባቢ ማህበረሰብ ጋር ጭምር ግጭት እየፈጠሩ ስለሆነ ወደ መጡበት አካባቢ  መመለስ እንደሚገባቸው ገልጸዋል።  ድንበር ዘለል አርብቶ አደሮቹ ይዘው የሚመጡት የቀንድ ከብት ብቻ ሳይሆን፤ ሕገ - ወጥ የጦር መሣሪያ ጭምር ስለሆነ በአካባቢው የፀጥታ ስጋት እየሆኑ ነው ያሉት ደግሞ ሌላው ተሳታፊ አቶ ኡሞድ ኡባንግ ናቸው። ስለሆነም አርብቶ አደሮቹ ወደ መጡበት እንዲመለሱ የክልሉና የፌዴራል መንግሥታት ሊሰሩ እንደሚገባ አሳስበዋል።  ለአንድ ቀን በተዘጋጀው በዚሁ የንቅናቄ መድረክ ላይ የፌዴራልና የክልሉ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችን ጨምሮ ከ250 የሚበልጡ ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል። የጋምቤላ ብሔራዊ ፓርክ በ1965 የተቋቋመ ሲሆን፣ በውስጡ 69 አጥቢ፣ 327 የአዋፍ፣ 490 በላይ እዕፅዋት ዝርያዎች ይገኙበታል። ፈላታ ከምዕራብ አፍሪካ ተነስቶ በማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክና በሱዳን አድርጎ ወደ ኢትዮጵያ የሚገባ የከብት አርቢዎች ቡድን ነው።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም