በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚፈጠሩ ግጭቶችን ለመፍታት በጥናት ላይ ተመስርቶ የተቀናጀ ስራ መስራት አለብን

54
አዲስ አበባ ታህሳስ 11/2011 ''በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚፈጠሩ ግጭቶችን በዘለቄታዊነት ለመቀነስ በጥናት ላይ የተመሰረተ የተቀናጀ ስራ መስራት አለብን'' ሲሉ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አመራሮች አስታወቁ። አመራሮቹ ለኢዜአ እንዳስታወቁት፤ ተማሪዎቹ የራሳቸው የህይወት መስመር ኖሯቸው አላማቸውን ከግብ የሚያደርሱበት አቅም እንዲኖራቸው የትምህርት ተቋማቱ በጥናት ላይ የተመሰረተ ቅንጅታዊ አሰራር መዘርጋት ይጠበቅባቸዋል። ተማሪዎቹ ከውስጣዊና ውጫዊ ጫናዎች ነፃ ሆነው እንዲማሩ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚፈጠሩ አስተዳደራዊና ውጫዊ የግጭት መንስኤዎች ተለይተው መፈታት እንደሚኖርባቸውም ተናግረዋል። በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ፈትየን ኣባይ በተለይም በማህበራዊ ድረ ገፆች የሚተላለፉ  መልዕክቶችን ተማሪዎች እንዴት መጠቀም እንዳለባቸው እንዲያውቁ መደረግ ይኖርበታል ብለዋል። ትክክለኛ የመረጃ ምንጮችን እንዴት ሊለዩ እንደሚችሉ ማሳወቅ ቅድሚያ ተሰጥቶት ሊሰራበት እንደሚገባ ገልጸዋል። ለዚህም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የግጭት መነሻ ምክንያቶችን፣ የቅድመ ግጭት መከላከል ስልቶችንና ድህረ ግጭት መፍትሄዎችን በትክክል ወደተማሪው የሚሰርጽበት ጥናት በቅንጅት መስራት እንዳለበት አስገንዝበዋል። በዚህ ዘርፍ የተማሪዎች ልዩ ልዩ አደረጃጀቶችና መምህራንም የሚሳተፉበት መሆን እንዳለበትም ገልፀዋል። በአዳማ ዩኒቨርሲቲ የትምህርት ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚዳንት ሙሉ ኪታባ በበለኩላቸው ተማሪዎቹ እውነትም ይሁን ውሸት ማንኛውንም መረጃ ከተመለከቱ በኋላ ወደ ግጭት እንዳይገቡ በቅድሚያ ምን ማድረግ እንዳለባቸው ከሚሰጠው የግንዛቤ ትምህርት በላይ ማስረዳት ያስፈልጋል ብለዋል። ''በአሁኑ ወቅት ፆታ፣ እድሜና የትምህርት ደረጃ ሳይለይ እንደ አገር ሁሉም ፖለቲከኛ የመሆን አዝማሚያ ይታይበታል'' ያሉት ምክትል ፕሬዚዳንቷ ለምን እንደመጣና በቀጣይ የሚያመጣው ችግር በማጥናት የመፍትሄ ሃሳብ መቀመጥ እንዳለበት ገልጸዋል። በአምቦ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ ትምህርት ክፍል ከሌሎች የትምህርት ክፍሎች ጋር በመሆን የግጭት መንስኤዎችና መፍትሄዎችን እንዲሁም ከአሁን በፊት እንደ አገር ጥቅም ላይ ሲውሉ የነበሩ ማህበራዊ በጎ ባህሎች ለምን ጠፉ እንዴትስ መመለስ ይቻላል የሚለውን የመፍትሄ ሃሳብ ጥናት በመስራት ላይ እንደሚገኝ ተጠቁሟል። የደባርቅ ዩኒቨርሲቲ መምህር ይመኝ አሰፌ በበኩላቸው መምህራን ተማሪዎችን በቅርበት በማስተማር፣ በችግሮቻቸው ላይ በማማከርና ጥሩ አመለካከት እንዲኖራቸው የማድረግ ትልቅ ሃላፊነት እንዳለባቸው ተናግረዋል። በትምህርት ተቋማቱ ፍትሃዊ አስተዳደራዊ ስርአት እንዲኖር የማድረግና ችግሮች ሲፈጠሩ በቀላሉ እንዲፈቱ ለማድረግ እንደሚሰሩ ገልጸዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም