የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሁለት አዋጆችን በአብላጫ ድምጽ አጸደቀ - ኢዜአ አማርኛ
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሁለት አዋጆችን በአብላጫ ድምጽ አጸደቀ
አዲስ አበባ ታህሳስ 11/2011 የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአስተዳደር ወሰንና የማንነት ጉዳዮች ኮሚሽንና የመከላከያ ሰራዊት አዋጆችን መርምሮ በአብላጫ ድምጽ አጸደቀ። የኢፌዴሪ የመከላከያ ሰራዊት አዋጅ ከምክር ቤቱ አባላት አንዳንድ ማስተካከያዎች ተደርጎበት እንዲጸድቅ አስተያየት ተሰጥቶበት በአዋጅ ቁጥር 1100/2011 በአንድ ድምጸ ተዓቅቦ በአብላጫ ድምጽ ጸድቋል። ምክር ቤቱ በአራተኛ ዓመት የስራ ዘመን 13ኛ መደበኛ ስብሰባው በውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች እና የህግ የፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴዎች ያቀረቡትን ረቂቅ አዋጅ መርምሮ አጽድቋል። የአስተዳደር ወሰንና የማንነት ጉዳዮች ኮሚሽን በራሱ የመወሰን ስልጣን ያልተሰጠው፣ የግጭት መንስኤዎችን ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ የሚያጠናና አማራጭ የመፍትሄ ምክረ ሃሳቦችን ለሚመለከታቸው አካላት የሚያቀርብ እንደሆነ ተገልጿል። ነገር ግን ኮሚሽኑ በአዋጅ ቁጥር 1101/2011 በ33 ተቃውሞ፣ በአራት ድምጸ ተዓቅቦና በአብላጫ ድምጽ ከመጽደቁ በፊት የምክር ቤቱን አባላት በሁለት ጎራ ከፍሎ አከራክሯል። በመጀመሪያ ረቂቅ አዋጁ በኅብረተሰቡ ዘንድ ውይይት ያልተደረገበት፣ የጥቂት አካላት ፍላጎት፣ ህገ መንግስቱን የጣሰና መሰረታዊ ዝንፈት ያለበት እንደሆነ ተገልጿል፤ ከአሁን ቀደም የጸደቁ አዋጆች ዋጋ እንዳስከፈሉም ተነግሯል። የአስተዳደር ወሰንና የማንነት ጉዳይ በህገ መንግስቱ መሰረት የፌዴሬሽን ምክር ቤት ምላሽ ሲሰጥበት የቆየ ሆኖ ሳለ የህገ መንግስቱን አንቀጾች ለአብነት አንቀጽ 39፣ 47፣ 48፣ 62፣ 81፣ 82ን በመቃረን የወጣና ተገቢነት የሌለው አዋጅ ነውም ተብሏል። በአገሪቱ ከወሰንና ማንነት ጋር በተያያዘ የሚነሱ ግጭቶች እንኳን ቢኖሩ የፌዴሬሽን ምክር ቤትን ማጠናከር እንጂ ስልጣኑን የሚጋፋ፣ የህዝቦችን የስልጣን የበላይነት የሚነፍግ፣ የስልጣን ክፍፍልን የሚጻረር ኮሚሽን ማቋቋም አያስፈልግል የሚል አስተያየትም ተሰጥቷል። የማንነትና የወሰን ጉዳይ በሁለቱ ክልሎች የሚፈታ፤ ካልተስማሙ ፌዴሬሽን ምክር ቤት ጣልቃ የሚገባበት ራሱን ለማጠናከር ጊዜያዊና ቋሚ ኮሚቴዎችን ማቋቋም የሚችልበት አሰራር እያለ ኮሚሽኑ መቋቋም እንደሌለበት ተገልጿል። ህገ መንግስት የሚጥስ ኮሚሽን እያቋቋምን ህገ መንግስቱ ይከበር የሚል ሞራል አይኖረንም፣ የኮሚሽኑ አባላት ገለልተኛ አይሆኑም፣ ወደባሰ ችግር ያስገባናል የሚል ስጋትም ቀርቧል። በህገ መንግስቱ አንቀጽ 48 ላይ ለክልሎች በተሰጣቸው ስልጣን መሰረት ኮሚሽኑን አናስገባም ቢሉ የሚፈጠረው ችግር ጸጸት ላይ ስለሚጥል መቋቋም የለበትምም ተብሏል። በሌላ በኩል ኮሚሽኑ መቋቋሙ ጊዜውን የጠበቀ፣ 'እስካሁን የበደልነውን ህዝብ የምንክስበት ህዝቡ ያመጣውን ለውጥ ቀጣይነት እንዲኖረው የሚያደርግ ነው' የሚል አስተያየት ቀርቧል። በኮሚሽኑ ይጣሳሉ ተብለው የቀረቡት የህገ መንግስቱ አንቀፆች ለአብነት አንቀጽ 81 ስለ ዳኞች አሿሿም፣ አንቀጽ 82 የህገ መንግስት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ አወቃቀር የሚገልጹ በመሆናቸው ከኮሚሽኑ መቋቋም ጋር የሚያገናኘው ነገር እንደሌለም ተገልጿል ከምክር ቤቱ አባላት ዜጎችን የሚያፍን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማንንም ሳናማክር በፍጥነት ስናደርግ የነበርን ሰዎች የዜጎችን መብት የሚያስከብር አዋጅ ሲወጣ ህዝብ ይወያይ ፈጠነ የሚል ሰበብ ማቅረብ ኢ-ሞራላዊ ነው የሚል አስተያየትም ተሰነዝሯል። የፌዴሬሽን ምክር ቤት የቀረቡለትን የማንነትና የወሰን ጉዳዮች ላይ ለበርካታ ዓመታት ምላሽ ስላልጠሰ ኮሚሽኑ አማራጭ ሃሳብ በማቅረብ እንደሚያግዘውም ተገልጿል። ከዚህ ባለፈም በህገ መንግስቱ ሽፋን በዜጎች ላይ የደረሰውን በደል ኮሚሽኑ ሳይንሳዊ ጥናት በማቅረብ የመፍትሄ ሃሳብ መስጠት የሚያስችል በመሆኑ መቋቋሙ ተገቢና ወቅቱን የጠበቀ ነው ተብሏል። የዜጎች መብት ሲጣስ፣ መብቶች ሲታፈኑ ለችግሩ መፍትሄ የሚያመጣ አደረጃጀት መፍጠር እንዳሚቻል በህገ መንግስቱ በግልጽ ተቀምጧል። የኮሚሽኑ መቋቋም ችግር ያመጣል፣ በህዝቦች መካከል የባሰ መቃቃር ያመጣል የሚለው ማስፈራሪያ መቆም እንዳለበትም ነው የተነገረው። የኮሚሽኑ አባላት በጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካኝነት ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚቀርቡ ሲሆን ሚዛናዊነታቸውና ገለልተኝነታቸው ተገምግሞ እንደሚሰየሙ ተገልጿል። የአስተዳደር ወሰንና የማንነት ጉዳዮች ኮሚሽን በምክር ቤቱ አባላት ሰፊ ውይይትና ክርክር ከተካሄደበት በኋላ በአዋጅ ቁጥር 1101/2011 በ33 ተቃውሞና በአራት ድምጸ ተዓቅቦ በአብላጫ ድምጽ ጸድቋል።