በስልጣን ላይ ያለው አመራርና ትውልዱ የቀድሞ ፕሬዝዳንት ግርማ ወልደጊዮርጊስን ፈለግ መከተል አለባቸው - ኢዜአ አማርኛ
በስልጣን ላይ ያለው አመራርና ትውልዱ የቀድሞ ፕሬዝዳንት ግርማ ወልደጊዮርጊስን ፈለግ መከተል አለባቸው
አዲስ አበባ ታህሳስ 10/2011 የቀድሞ ፕሬዝዳንት ግርማ ወልደጊዮርጊስ ሰላምና ፍቅር የሰፈነባት ሀገርን በመፍጠር አርአያ የሆኑ መሪ በመሆናቸው በስልጣን ላይ ያለው አመራርና ትውልዱ የእሳቸውን ፈለግ መከተል እንዳለበት ተገለፀ። ኢዜአ ያነጋገርናቸው አስተያየት ሰጪዎች ፕሬዚዳንት ግርማ ለአገራቸው ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ በትጋት የሰሩ መሪ እንደነበሩ ገልፀዋል። በኢትዮጵያ ስካውት ማህበር የስራ አስፈፃሚ ኮሚሽነር ሻምበል ጳውሎስ ወልደገብርኤል እንዳሉት፤ አቶ ግርማ ከአገር መሪነት ባሻገር በተለያዩ የበጎ ፈቃድ አገልግሎቶች የተሳተፉ ናቸው። ለኢትዮጵያ ስካውት ማህበርም አባታዊ አመራር በመስጠት የልጆችንም ፍላጎት በማነሳሳት ትልቅ አስተዋፅኦ እንዳበረከቱ ተናግረዋል። በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከልም እርቀ ሰላም እንዲኖር ብርቱ ጥረት ያደረጉ ታላቅ መሪ እንደነበሩ አስታውሰዋል። ፕሬዚዳንት ግርማ ሌሎች ሊከተሉት የሚገባን በሰላምና በፍቅር መምራትን ያስተማሩና ተምሳሌት የሆኑ መሪ እንደነበሩም አብራርተዋል። የቀድሞው ፕሬዚዳንት ግርማ ከአለማዊው ህይወታቸው ባሻገር ክርስትያናዊ ስነምግባርን የተላበሱ በህገ እግዚአብሄር የተመሩና የተጓዙ መሪ ነበሩ ያሉት ደግሞ የምስራቅ ሀረርጌ ሀገረስብከት ሊቀጳጳስ ብፁእ አቡነ ሰላማ ናቸው። ፕሬዚዳንቱ ከንጉሳዊው አስተዳደር ጀምሮ እስከ አሁኑ መንግስት ድረስ ለበርካታ ዓመታት በትጋት የሰሩ መሪ እንደነበሩ ተናግረው ትውልዱ የሳቸውን መንገድ ተከትሎ መሄድ እንደሚገባው ነው ያስረዱት። የዳውዲ ቦሆራ ኮሙዩኒቲ የተሰኘው የእስልምና ማህበር ፕሬዚዳንት መሀመድ ሁሴን በበኩላቸው ከግርማ ወልደጊዮርጊስ ጋር ትውውቃቸው ፕሬዚዳንት ሳይሆኑ በፊት እንደነበርና ጥሩ ቤተሰባዊ መስተጋብር እንዳላቸው ነግረውናል። ፕሬዝዳንት ግርማ ለማህበሩ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዳበረከቱና ማህበሩን ሲደግፉ እንደነበር ነው የገለፁት። አገሪቱን እየመሩ ያሉ ባለስልጣናትም እንደ አቶ ግርማ አገርን በትጋት ቢመሩ አገሪቱ ተጠቃሚ ትሆናለች ብለዋል። ታህሳስ 5 ቀን 2011 ዓ.ም በ95 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት የቀድሞው ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደጊዮርጊስ በተለያዩ የኃላፊነት አገራቸውን አገልግለዋል። ለ12 ዓመታትም የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት በመሆን ኃላፊነታቸውን ተወጥተዋል።