በኢትዮጵያ የባህል ህክምና ረቂቅ ፖሊሲ ተዘጋጀ - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ የባህል ህክምና ረቂቅ ፖሊሲ ተዘጋጀ
አዲስ አበባ ታህሳስ 10/2011 በኢትዮጵያ የባህል ህክምና ፖሊሲ ረቂቅ መዘጋጀቱ ተገለጸ። ረቂቅ ፖሊሲውን ያዘጋጁት የኢትዮጵያ የምግብ፣ መድሃኒትና ጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለስልጣን እና የኢትዮጵያ ማህበረሰብ ጤና አጠባበቅ ኢንስቲትዩት ከተለያዩ የሚመለከታቸው ሌሎች ተቋማት ጋር በመተባበር ነው። ረቂቅ ፖሊሲውን ማዳበር ይቻል ዘንድ የተጨማሪ ግብኣት የማሰባሰበ ዓላማ ያለው አውደ ጥናት ዛሬ አዲስ አበባ ውስጥ ተካሂዷል። የባህል ህክምና በዓለም አቀፍ ደረጃ ከ5 ሺህ ዓመት በፊት ጀምሮ የሚታወቅ የጤና ዘርፍ ነው። በተለይም በቻይና፣ ህንድ፣ የተለያዩ የላቲን አሜሪካና አፍሪካ አገራት የባሀል ህክምና ሰፊ አውቅናና አገልግሎት እንዳለው ይነገራል። በኢትዮጵያም ከ80 በመቶ በላይ የሚሆነው ሕዝብ የባህል ህክምና ተጠቃሚ እንደሆነ መረጃዎች ይጠቁማሉ። ያም ሆኖ ግን በኢትዮጵያ የባህል ህክምና የሚመራበት የሕግ ማዕቀፍ ባለመኖሩ የተነሳ ዘርፉን በሚገባው መጠን በማልማትና በማሳደግ አገሪቱን ተጠቃሚ ማድረግ እንዳልተቻለ ይነገራል። ለዘርፉ ተገቢው ትኩረት ባለመሰጠቱ ዘርፉ እንዳያድግ ከማድረግ ባሻገር ህገ-ወጥ የባህል ህክምና እንዲስፋፋና የዜጎች ጤና ደህንነት አደጋ ላይ እንዲወድቅ እንደዚሁም በመስኩ የሰለጠነ የሰው ኃይል እንዳይገኝ እንዳደረግም ይነሳል። የኀብረተሰብ ጤና አኒስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ኤባ አባተ የገለፁትም ይህንኑ ነው። እንደ ዶክተር ኤባ ገለፃ፤ በኢትዮጵያ የባህል ህክምናን በማጠናከር የተሻለ ተጠቃሚ ለመሆን የሚያስችል ምቹ ሁኔታ ቢኖርም በሚፈለገው መጠን ተጠቃሚ መሆን አልተቻለም። ለዚህ ደግሞ ቁልፍ ችግር ዘርፉ የሚመራበት ፖሊሲ አለመኖር መሆኑን ጠቅሰዋል። ይህንን ሁኔታ ለመቀልበስና ከዘርፉ የሚገባውን ጥቅም ለማምጣት ኢኒስቲትዩቱ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን ፖሊሲ፣ አዋጅና ስትራቴጂ እያዘጋጀ ነው። ይህም የባህል ህክምናው ዋና ዋና ችግሮች በመፍታት ከመደበኛ ጤና አገልግሎት ጎን ለጎን ተጠቃሚ የሚኮንበት እድል ይፈጥራል ባይ ናቸው። ''በ1993 ዓ.ም ወጥቶ በነበረው የጤና ፖሊሲ ውስጥ የባህል ህክምና የሚደግፉ ነገሮች ቢካተቱም ወደ ተግባር መቀየሩ ላይ ክፍተቶች ነበሩ" ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ በአሁኑ ወቅት የጤና ፖሊሲው የባህል ህክምናን ታሳቢ ባደረገ መልኩ እየተከለሰ በመሆኑ ውጤት ይገኝበታል ትብሎ ይጠበቃል ሲሉም አብራርተዋል። እንደ ዶክተር ኤባ ገለጻ የባህል ህክምናው የሚመራበት ፍኖተ ካርታ ዝግጅት የተጠናቀቀ በመሆኑ በቅርቡ ለጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ቀርቦ ስራ ላይ የሚውልበት ሁኔታ ይመቻቻል። ዘርፉ ውጤታማ እንዲሆን የግብርና፣ ትምህርት ተቋማትና በባህል ላይ የሚያተኩሩ ተቋማት በቅንጅት መስራት እንደሚኖርባቸውም አጽንኦት ሰጥተዋል። በኀብረተሰቡ ዘንድ ስለ ባህል ህክምና ያለው የተዛባ አመለካከት ችግር ሌላው ማነቆ መሆኑን ገልጸው ወደፊት ግንዛቤውን ለማስፋት በትኩረት መስራት እንደሚገባም ገልፀዋል። በባህል ህክምና ዘርፍ ጠቃሚ ምርምር ሥራዎችን ለማከናወንና አገር በቀል የህክምና እውቀትን በሚቻለው መጠን ለአገልግሎት ለማብቃት የሚያስችል የፋይናንስ ድጋፍ ሊኖር እንደሚገባም ዶክተር ኤባ አሳስበዋል። የኢትዮጵያ የምግብ፣ መድሃኒትና ጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ከይሬዲን ረዲ በበኩላቸው የባህል ህክምና በአግባቡ ከተሰራበት በጤናው መስክ ከሚያበረክተው አስተዋጽኦ ባሻገር የውጭ ምንዛሬ፣ የኢንቨስትመንትና የሥራ ዕድል በመፍጠር በኩል የጎላ ሚና ይጫወታል። ዘረፉን በምርምርና ጥናት በማስደገፍ ከመደበኛ የጤና አገልግሎት ስርዓት ጋር ማቀናጀት ወሳኝ መሆኑን ጠቁመው ለዚህም የሕግ ማዕቀፎች ማዘጋጀት ጠቃሚ መሆኑ ታምኖበት ወደ ሥራ ተገብቷል ነው ያሉት። ፖሊሲውን ጨምሮ የተለያዩ የሕግ ማዕቀፎች መዘጋጀታቸው የባህል ህክምና እውቀትና መረጃዎች ተመዝግበውና ተጠብቀው እንዲቆዩ በማድረግ በኩል አወንታዊ ሚና እንደሚኖረው አብራርተዋል። እንደ ዶክተር ከይረዲን ገለጻ ዘርፉን በሚገባው መጠን ለማሳደግና ጥቅም ላይ ለማዋል የባህል መድሃኒት ግኝቶችን የባለቤትነት መብት ማስጠበቅ ይገባል። በአውደ ጥናቱ ላይ የዓለም የጤና ድርጅትን በመወከል ንግግር ያደረጉት አቶ መንግስተአብ ወልደአረጋይ የባህል ህክምናን በተመለከተ የሚደረጉ የምርምር ስራዎች ወደ ተግባር ለመቀየር መስራት ያስፈልጋል ብለዋል። የዓለም የጤና ድርጅት ዘርፉ በህግና ስርዓት እንዲመራ ጽኑ አቋም መያዙን አስረድተው በኢትዮጵያ የተዘጋጀው የባህል ፖሊሲና ሌሎች ማዕቀፎች ተግባራዊ እንዲሆኑ ድርጅቱ ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል። አውደ ጥናቱ ነገም እንደሚቀጥል ከወጣው መርሃ ግብር ለማወቅ ተችሏል።