ቀጥታ፡

የቀድሞው ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደጊዮርጊስ አስከሬን የመጨረሻ ሽኝት ስርዓት ተከናወነ

አዲስ አበባ ታህሳስ 10/2011 ለቀድሞው ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደጊዮርጊስ አስከሬን የመጨረሻ ሽኝት ስርዓት በአዲስ አበባ ሚሊኒየም አዳራሽ ተከናወነ። በስነ-ስርዓቱ ላይ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴን፣ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን፣ የተለያዩ አገራት አምባሳደሮችን ጨምሮ በርካታ የህብረተሰብ ክፍሎች ተገኝተዋል። በዚሁ ወቅት በተነበበው የቀድሞው ፕሬዚዳንት ግርማ የህይወት ታሪክ ላይ በህይወት ዘመናቸው ያከናወኗቸው በርካታ ተግባራት ተነግረዋል። አብዛኛውን እድሜያቸውን በመንግስትና ህዝብ አገልግሎት ተግባር ያሳለፉት የቀድሞው ፕሬዚዳንት በኢትዮጵያ የፖለቲካ፣ ማህበራዊና ምጣኔ ኃብታዊ ለውጥ እንዲመጣ ሌት ተቀን የደከሙ የአገር ባለውለታ መሆናቸውም በታሪካቸው ላይ ተገልጿል። በቀዳማዊ ኃይለስላሴ ዘመነ መንግስት እና አሁን ባለው ፓርላማ አባል በመሆን ህዝባቸውን ያገለገሉት የቀድሞው ፕሬዚዳንት ግርማ በተለይ በንጉሱ ዘመን ወደፓርላማ ለመግባት የወሰኑት በወቅቱ በአገሪቱ ተንሰራፍቶ የነበረው ድህነትና የህዝብ መከራና ስቃይ ስላስቆጫቸው እንደነበር በህይወት ታሪካቸው ላይ ተወስቷል። በወቅቱ የተወዳደሩትም አዲስ አበባ ልደታና ቀራኒዮ  ወረዳ ሲሆን በምርጫውም 800 ድምፅ በማግኘት አሸንፈው በፓርላማው መቀመጫ አግኝተዋል፤ ፕሬዚዳንት ሆነውም ለመመረጥ በቅተዋል። የቀድሞው ፕሬዚዳንት የአካባቢ ጥበቃና የአርንጓዴ ልማት ጉዳይ ከግማሽ ምእተ ዓመት በፊት ያሳሰባቸውና ችግሩንም ለመከላከል በትጋት የሰሩ ነበሩ። በንጉሱ ዘመን ፓርላማ ቆይታቸውም ታግለው ለውጤት ከበቁባቸው ተግባራት መካከል እስከ ህይወት ፍፃሜያቸው ድረስ ሲሟገቱለት የኖሩት  የአረንጓዴ ልማትና  የጥብቅ ደን ጉዳይ ይጠቀሳል። በዚህ ከፍተኛ ተቃውሞ በነበረበት አጋጣሚ ባከናወኑት ያላሰለሰ ትግልም የደን ልማትና ጥበቃን የተመለከተ ህግ እንዲወጣ አድርገዋል። ኢትዮጵያ የዓለም አቀፉ ፓርላማ ህብረት አባል ተደርጋ እንድትመረጥም ትልቅ ሚና መጫወታቸውን የህይወት ታሪካቸው ላይ ተመልክቷል። የዓለም ፓርላሜንታሪ ፕሬዚዳንት ሆነውም አገልግለዋል። ፕሬዚዳንት ግርማ በደርግ መንግስት የኤርትራ ሰላም ልኡክ ምክትል ኮሚሽነር ተደርገው አስከ 1983 ዓም ድረስ በኤርትራ ክፍለ አገር አገልግለዋል። በኤርትራ ባሳለፉት ረጅም የሥራ ዓመታት የኤርትራን ህዝብ በቅርብ ለማወቅ ከመቻላቸውም በላይ የህዝቡን እውነተኛ ስሜትና ፍላጎት በአግባቡ ለመረዳት አስችሏቸዋል። በመሆኑን የኢትዮጵያና ኤርትራ ህዝቦች በቋንቋ፣ ባህል፣ በሃይማኖትና ሌሎች በርካታ ጉዳዮች የሚቀራረቡ ጠንካራ ወዳጅነትና አንድነት መፍጠር የሚችሉ ናቸው በማለት ብዙ ጊዜ ይናገሩ አንደነበርም ተመልክቷል። እናም በሁለቱ አገራት መካከል ጠንካራ ሰላማዊ ግንኙነት እንዲፈጠር ከተለያዩ አካላት ጋር በመሆን ያከናወኗቸው ተግባራት በታሪክ የሚወሳ መሆኑም ተጠቅሷል። በኢትዮጵያ የደን ልማትን ለማስፋፋት ማህበራትን በማቋቋም ጭምር የተለያዩ አመርቂ በጎ ተግባር መፈፀማቸውም በህይወት ታሪካቸው ተወስቷል። ለምህረትና ይቅርታ ትልቅ ስፍራ የሚሰጡት የቀድሞው ፕሬዚዳንት ግርማ በአገሪቱ በተለያዩ ምክንያቶች ማረሚያ ቤት የገቡ ዜጎች ይቅርታና ምህረት ሊደረግላቸው ይገባል የሚለውን አስተሳሰብ ያራምዱ እንደነበርም ታሪካቸው ያስረዳል። በመንግሰት ሥራ ኃላፊነት ዘመናቸውም የደርግ ባለስልጣናትን ጨምሮ የተለያዩ ታራሚዎች በምህረትና ይቅርታ እንዲለቀቁ አድርገዋል። የቀድሞው ፕሬዚዳንት ከፖለቲካ ኃላፊነት ባሻገር የሰብአዊ ድጋፍን ጨምሮ በተለያዩ ማህበራዊ የበጎ ተግባራቸው አርዓያ ሊሆኑ የሚችሉ በርካታ ተግባራትን ያከናወኑ ባለውለታ መሆናቸውም በህየወት ታሪካቸው ላይ ተዘርዝሯል። በስነ -ስርዓቱ ላይ በቅርብ የሚያውቋቸው፣ የሥራ ባልደረቦቻቸውም የሚያውቁትን አካፍለዋል። ከሽኝቱ ስነ-ስርዓት በኋላ የቀብር ስርዓታቸው በቅዱስ ካቴድራል ስላሴ ቤተክርስቲያን በኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትሪያርክ አቡነ ማቲያስ በሚመራ ስርዓተ ፀሎት ይፈፀማል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም